



==============
ህዳር 19/2016
የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ የባለድርሻ አካላት መድረክ አካሄደ!!
በዛሬው ዕለት የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ የ2016 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም እና የሰልጣኝ ቅበላ ንቅናቄ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሄደ።በመድረኩ የቀበሌ ሊቀመናብርት፤ሱፕርቫይዘሮች፤የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ር/መምህራን ፤የእዣ ወረዳና የአገና ከተማ አስተዳደር አመራሮች የተገኙ ሲሆን ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ በኮሌጁ ዲን አቶ አስቻለው ስባኒ ቀርቧል።በቀረበው የውይይት ሰነድ መነሻነት ተሳተፊዎች በርካታ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ እኩል ሌላኛው አማራጭ መሆኑን በማንሳት አሁን ካለንበትና ከወደፊት የሀገራችን የስራ ዕድል አንፃር በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መሰልጠን ተመራጭ መሆን እንደሚገባው ገልፀዋል።የቀበሌ ሊቀመናብርት በበኩላቸው ከየትኛውም ስራ አስቀድሞ የወጣቱ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ኮሌጅ የሚመጡበት ሁኔታ ላይ ከወረዳ አመራር እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ በከፍተኛ ርብርብ ሊሰራ ይገባል ያሉ ሲሆን ወላጆች፤ሙህራንና የወረዳችን ተወላጅ ባለሀብቶች ለዚህ ተግባር መሳካት የበኩላቸው መወጣት ይገባቸዋል ሲሉም አክልዋል።የውይይት መድረኩ የመሩት የእዣ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ ከወረዳ ማዕከል እስከ ቀበሌ ኮማንድ ፖስት ተዋቅሮ በየዕለቱ የሚገመገም ተግባር መሆኑን ገልፀው የወጣቱ የነገ ህይወት የሚቀየረው የሙያና ክህሎት ባለቤት ሲሆን መሆኑን በመረዳት እንዲሁም ወጣቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በማጠናቀቅ ስራ በመፍጠር የራሱ ገቢ እየፈጠረ በቀጥታ አሁን ያጣውን የዩኒቨርሲቲ መግባት ዕድል የሚያገኝበት መስመር መሆኑ መገንዘብና ማስገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።ዛሬ ላይ በዚህ ኮሌጅና በወረዳችን ባሉ የመንግስት ሴክተሮች የዲግሪ/ማስተር ባለሙያዎች መነሻቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና መሆኑን እንዲሁም ዛሬ ከፍተኛ የሆነ ሀብት የፈጠሩ የብረታ ብረት፤የእንጨት ስራ፤ኤሌክትሮኒክስ፤ኮንስትራክሽንና አውቶሞቲቭ ስልጠና የሰለጠኑ ከዚሁ ኮሌጅ የወጡ ተመራቂዎች ማየት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጠቀሜታ በቂ ማሳያ ነው ሲሉ አብራርተዋል።በመጨረሻም እያንዳንዱ ተሳታፊ ተግባርና ሃላፊነት በመከፋፈል የስራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል።






©2023. የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ከአገና ኮንስትራክሽን እና ኢደስትሪያል ኮሌጅ ጋር በመተባበር. All Rights Reserved.