የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

=============================================

ታህሳስ 02/2016
ተማሪዎች በሁሉም የትምህርት መስኮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑና በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ወደ ፈጠራ ተግባር መቅየር እንዲችሉ ትኩረት ሰጥተው መማር እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው ከእዣ ወረዳ ሳ/ኢ/ቴ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በእዣ ወረዳ ሸኸረሙ ቀበሌ በየዋኸንየ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትቤት ዞናዊ የሳይንስ ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል ።
የጉራጌ ዞን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ እንደገለጹት የሳይንስ ሳምንት ዋናው አለማው ከሳይንስ ጋር የተያያዙ የፈጠራ ስራዎችን የበለጠ ለማጉላትና ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች በሁሉም የትምህርት መስኮች ተወዳዳሪና የፈጠራ ባለቤት እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥተው በመማርና በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ወደ ፈጠራ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አቶ ደምስ ገብሬ ገልጸዋል ።
የፈጠራ ስራዎች በቀላሉ የሚመጡ አይደሉም ያሉት አቶ ደምስ ከፈጠራ ጽንስ ሀሳብ በመነሳት ወደ ተግባር ለመግባት በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙና ይህንንም በብቃት ማለፍ ይገባል ብለዋል።
በየጊዜው የሳይንስ ሳምንት በማክበር ፣ የሳይንስ ክበቦችን በመመስረትና የፈጣራ ሰዎችን እንዲበረታቱ በትኩረት ይሰራል ብለዋል አቶ ደምስ ።
የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተጠመቀ በርጋ እንደተናገሩት ትምህርት የአንድ ሀገር እድገትና ስልጣኔ በር ከፋች መሳሪያ እንደሆነና ይህም ሊሆን የሚችለው በጥናትና ምርምር ፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለሀገር እድገትና ስልጣኔ ሁለንተናዊ ፋይዳ ያለው መሆን እንዳለበት ገልጸዋል ።
አሁን የተጀመረው በትምህርት ቤት ደረጃ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ክበብ ምስረታ በማጠናከርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ተመራማሪ ትውልድ መፍጠር ይገባል ።
የእዣ ወረዳ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ረኢማ ሙህታጅ በበኩላቸው በሳይንስና ቴክኖሎጂ በፈጠራ ስራዎች ዘርፍ የፈጠራ አቅም ያለቸውን ተማሪዎች በመደገፍ በማበረታታትና በማብቃት ለማህበረሰቡ አግልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል ።
ከነዚህም የማህበረሰቡን ችግር ፈቺ የሆኑ የቆጮ መፋቂያ ፣ የአሚቾ መከትከቻና የገብስ መውቂያ ለአብነት የጠቀሱት ኃላፉዋ እንዲሁም የዌብሳይት ማበልጸግ ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል ።
እንደ ወይዘሪት ረኢማ ሙህታጅ ገለጻ እውቀቱ በቴክኖሎጂ የዳበረና ከእራሱ አልፎ አገሩን የሚጠቅም ዜጋ ለመፍጠር ትምህርት ቤቶች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል ።
በእዣ ወረዳ የዋኸንየ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጀንበር ክብሩ እንደተናገሩት ተማሪዎች ያለቸውን ተሰጦ በሳይንሱ በመታገዝ ወደ ተግባር መቀየር እንዲችሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ከበብ ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል ።
በዚህም በርካታ ተማሪዎች ቴክኖሎጂዎችን አሻሽሎ በመቅዳትና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
የሳይንስ ሳምንት በተከበረበት ወቅት ያነጋገርናቸው የፈጠራ ስራ ካቀረቡ ተማሪዎች መካከል አቶ ዳንኤል መንግስቱ ከአገና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አብድል መጅድ ሀድራ ከአገና 01 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኙበታል ።
ተማሪዎቹ የቾክ ማምረቻ እና ተራራዎችን በቀላሉ መንግድ መውጣት የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎችን መስራታቸውን ገልጸዋል ።
በዛሬው የሳየወንስ ሳምንት ማስጀመሪያ ሲከበር በተማሪዎች የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ ፣ ግጥሞች ፣የቤተ ሙከራ ጉብኝት እና የጥያቄና መልስ ውድድር እንዲሁም የተማሪዎች ጭውውት ተካሂደዋል ።
እንዲሁም የእውቅና ሰረተፍኬት የተሻለ የፈጠራ ስራ የሰሩ ተማሪዎች ፣መምህራኖች ፣ትምህርት ቤቶች ፣ጥያቄና መልስ ያሸነፉ ተማሪዎች የመጽሐፍና የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።
በመድረኩም የዞኑ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊና ባለሙያዎች ፣የወረዳው የትምህርት ጽህጸት ቤት ኃላፊዎች ፣የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።