የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

=============================================================

ጥቅምት28/2016ዓ.ም
================
የጉራጊኛ ቋንቋ በስርዓተ ትምህርት ተካቶ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው የጉራጊኛ ቋንቋ በቅድመ አንደኛ ደረጃ አንድና ደረጃ ሁለት ለማስተማር የተዘጋጀ የመጽሐፍት ትውውቅና የአሰልጣኞች ስልጠና ከዞኑ የተወጣጡ የቅድመ መደበኛ መምህራንና ሌሎች ባድርሻ አካላት የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ከጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በተሰጠበት ወቅት ነው።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በስልጠናው ወቅት እንደገለጹት አምና በ20 ቅድመ በመደበኛ ጣቢያዎች ላይ የጉራጊኛ ቋንቋ የሙከራት ትምርህት ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው በተያዘው በጀት ዓመት በሁሉም የመንግስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የማስፋት ስራ ይሰራል።
ከዚህም በተጨማሪ አምና በቅድመ አንደኛ ደረጃ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች በተያዘው የትምህርት ዘመንም የ1ኛ ክፍል የሙከራ ትምህርት በ18 ትምህርት ቤቶች ላይ እንደሚሰጥ ኃላፊው አብራርተዋል።
አቶ መብራቴ አክለውም ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ አካባቢያቸውን፣ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን የማወቅና የሚማሩት ትምህርት በቀላሉ በመረዳት ውጤታቸው ያማረና በስነ ምግባር የታነጹ በማድረጉ ረገድ እገዛ እንዳለው ተናግረዋል።
የጉራጊኛ ቋንቋን በስርዓተ ትምህርት አካቶ መሰጠቱ የመጀመሪያ በመሆኑ ለውጤታማነቱ የወላጆች፣ የመምህራንና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው ሲሉ መልዕታቸውን አስተላልፈዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስን ገብሩ በበኩላቸው የጉራጌ ማህበረሰብ የበርካታ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ባለቤት ሆኖ ሳለ ቋንቋው በማልማቱ ረገድ መዘግየቱን ገልጸው አሁን ጉራጊኛ ቋንቋ ለማልማት ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ዩኒቨርስቲው ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ዶ/ር ዮሐንስ አክለውም በቀጣይ የጉራጊኛ ቋንቋ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ በጥናትና ምርምር የማገዝ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቋንቋና ስነ ጥበብ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ባህሩ ሊላጋ እንዳሉት የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ በመምሪያው በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይቷል ብለዋል።
በዛሬው ዕለትም የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱ ለቋንቋው ማልማት ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
በስልጠናው ወቅት አግኝተን ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎችም እንደገለጹት ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉ ለመማር ማስተማር ሂደቱ በጣም እንደሚያግዝና ከህጻናት ጋር በቀላሉ ተግባቦትን ይፈጥራል።
ይህ ስልጠና በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በዞኑ የጉራጊኛ ቋንቋ በማስተማር ተሳትፎ ለሚያደርጉ ለ722 የቅድመ መደበኛ መምህራኖች እንደሚሰጥ ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመጨረሻም የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የዞኑ የትምህርት ስራ ለማገዝ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።