
===========================================
የገረሙጀ አትርፎ ደብረ-ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን
የገረሙጀ አትርፎ ደብረ-ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል የሚገኘው በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ሲሆን, ከዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ በ52ኪ.ሜ እንዲሁም ከወረዳው ዋና ከተማ አገና በ10ኪ.ሜ ርቀት ላይ በስተምስራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ የገረሙጀ አትርፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን በእዣ ወረዳ ከሚገኙ ጥንታዊ ቤተ-ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ይህ ቤተ-ክርስቲያን የተሰራው በአፄ የግዛት ጊዜ ተሰርቷል የሚል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በንጉስ የግዛት ማስፋፋት ምክኒያት የአካባቢው ሀገር ገዢ ተደርገው የተሾሙት ሶር ሚካኤል የተባሉት ግለሰቡ 1880ዎቹ አካባቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያንን እንደቆረቁሩ ይነግርላቸዋል፡፡ ቤተ-ክርስቲያኑ 4 ጊዜ ያህል ተሻሽሎ ተሰርቷል፡፡ከዳስ ጀምሮ የሳር ክዳን፣የቆርቆሮ ክዳን ቤቶችና ህንፃ ቤተ-ክርስቲያኑ ያለፈባቸው ደረጃዎች ሲሆን ህንፃው ህዳር 7/1989ዓ.ም በጉራጌ ከንባታና ሀድያ ሀገር ስብከት ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከጼዲቅ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ይህ ህንፃ የተገነባው የመጀመሪያው ቤተ-ክርስቲያን ከነበረበት ቦታ 500ሜትር ያህል ርቀት ወረድ ብሎ በሚገኝ ሰፊ ሜዳ ላይ ሲሆን እጅግ ዘመናዊና መንፈሳዊ ትምህርት መስጫ ካቴድራል አለው፡፡ህንፃው ተገንብቶ ካለቀ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ወደዚህኛው ህንፃ የገባ ሲሆን በቀድሞው ቤተ-ክርስቲያን/ግቢ/ደግሞ የባለእግዚአብሔር እና የሚካኤል ታቦቶች ይገኛሉ፡፡በአዲሱ ህንፃ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተጨማሪ የማሪያም ታቦት ይገኛል፡፡በአጠቃላይ በቤተ-ክርስቲያኑ ያለው ሲሆን, በሙዝየሙ በርካታ ታሪካዊና እድሜ ጠገብ የሆኑ ጥንታዊ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም ቅርሶች መሀከል ከ300 ዓመት በፊት ሲያገለግሉ የነበሩ መስቀሎች፣በደጅ አዝማች ባልቻ የተበረከቱ መስቀሎች፣የ739ዓመት እድሜ ያላቸው ጥንታዊ የነሀስና የብር ፅዋ፣የሰጎን እንቁላል፣በገናዎች፣ውጅግር የተባሉ የጦር መሳሪያ፣ከንሀስና ከእንጨት የተሰሩ መስቀሎች፣ፅናፅኖች፣መፅሐፍ ቅዱስ፣ድርሳነ ሚካኤል፣ታምረ ማሪያም፣ ጥንታዊ ልብሰተ ክህኖት እና ሌሎችም ቅርሶች ይገኛሉ፡፡በአገራችን በድምቀት ከሚከበሩ የቤተክርስቲያን በዓላቶች መካከል አትርፎ ደብረ ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከግንባር ቀደሞች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡የአትርፎ ደብረ-ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ዓመታዊ ከሚከበሩ ክብረ በዓላት ጥር 18 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ከዚህ የተነሳ የጥር 18 በዓል ግን አሁን የደቡብ ቁልቢ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡በክብረ በዓሉ እለት የሚገባው የስለት አይነትና መጠን በጣም ከፍተኛ ነው፡፡በአሉን ለማክበር ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የሀገራችን ከተሞች የሚመጣው በህዝብና በመኪና ብዛት አካባቢውን ለሁለት ቀናት ሞቅ ያለች ከተማ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ በዓሉን ለማክበር በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችና የውጭ ሀገር ዜጎችም ወደዚህ ስፍራ ይመጣሉ፡፡የቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀጳጳስ የጉራጌ ሀገር ስብከት ሊቀጳጳስ ቅዱስ አቡነ መልከ ፄዲቅ በበአሉ አከባበር ከመገረማቸው በላይ የበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ድምቀት የሰውና የመኪና ብዛት እንዲሁም የሚገባው ስለት ብዛት ካስተዋሉ በኋላ ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል የሚል ስም ሰጥተውታል፡፡ እንግዲህ ውድ አንባቢያን ይህንን ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ቅርሶች እንድትጎበኙ መልዕክታችን እናስተላልፋለን፡፡በመጨረሻ አስተያየት ሆነ ጥያቄ ካላቸሁ በስልክ ቁ.0113290217 ሆነ በአካል እ/ወ/ባ/ቱ//ፅ/ቤት በመቅብ መስጠት ትችላላችሁ፡፡