
================================
ግንቦት12/2016ዓ.ም
================ በጉራጌ ዞን “ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ሀሳብ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ንጽህና እንዲጠብቅ የተጠናከረ ስራ በመሰራቱ በሀገሪቱ የተጀመረውን “ጽዱ ኢትዮጵያን እንፍጠር” ንቅናቄ ቀድሞ ማሳካት እንደተቻለ የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በዞኑ እዣ ወረዳ በቆጠር ገድራ ቀበሌ ሙዳ መንደር እና በቸሃ ወረዳ አዘር ቀበሌ ቆረሚያ ሁለት መንደር ከአይነ-ምድር ነፃ መሆናቸውን በማረጋገጥ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ ተመርቀዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ያስጀመሩት ጽዱ ኢትዮጵያ እንፍጠር ንቅናቄ የዞኑ አመራሮችና የጤናው ሴክተር ባለሙያዎች በመቀላቀል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ዞኑ ቀደም ብሎ “ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ሀሳብ ህብረተሰቡ የአካባቢውንና የግሉ ንጽህና እንዲጠብቅ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ሲሰራ በመቆየቱ ጽዱ መንደር፣ ቀበሌ፣ ወረዳና ዞን ለመፍጠር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በዚህም በዞኑ እዣ ወረዳ በቆጠር ገድራ ቀበሌ ሙዳ መንደር እና በቸሃ ወረዳ አዘር ቀበሌ ቆረሚያ ሁለት መንደር ነዋሪዎች የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤቶች እየተጠቀሙ መሆናቸወንና አካባቢዎቹ ከአይነ-ምድር ነፃ መሆናቸውን በማረጋገጥ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ መመረቃቸውን ለተግባሩ መሳካት ማሳያ መሆኑን አቶ አየለ ገልጸዋል፡፡
ንጽህናው የሚጠብቅ ሰው ከሚያገኘው ማህበራዊና ኢኮሚያዊ ፋይዳው በተጨማሪ በማህበረሰቡም ዘንድ ከበሬታን እንደሚያገኝ የገለጹት አቶ አየለ ይህንንም ይበልጥ ውጤታ ለማድረግ በዞኑ አብዛኛው ማህበረሰብ የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤቶች ተጠቃሚ ቢሆኑም ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና የጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ለዕመንጎ በፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹት ጽዱ መንደር፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል መፍጠር ጽዱ ሀገር በመፍጠር ሀገርን ማስከበር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴር ደ/ር አብይ አህመድ ጽዱ ኢትዮጵያ መፍጠር የሚል ንቅናቄ ከማወጃቸው በፊት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአንዳንድ ወረዳዎች ጽዱ ኢትዮጵያ ለመፍጠር ከፍተኛ የንቅናቄ ስራ መስራት በርካታ ከአይነ ምድር ነጻ መንደሮች፣ ቀበሌዎችና ወረዳዎች መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ዛሬ ከአይነ-ምድር ነጻ በመሆናቸውን ተረጋግጠው በይፋ የተመረቁ በእዣና በቸሃ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ መንደሮች መረጃ እንደሚያሳየው ህብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ መጸዳጃ ቤት የሚጠቀም ቢሆንም በተወሰነ ደረጃ የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤት የማይጠቀሙ ማህበረሰቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አቶ ፍሰሃ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሪት ቃልኪዳን አሳልፍና ወ/ሮ ትግሉ ሰፋ የእዣና የቸሃ ወረዳዎች ጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ የሴቶች የልማት ህብረት፣ እድሮች፣ ተዋቂ ግለሰቦችና የሃይማኖት አባቶች ተጠቅመው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሰፊው በመስራታቸው ህብረተሰቡም በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎ የግሉና የአካባቢው ንጽህና መጠበቅ እንዲሁም የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤቶች በመጠቀም ከአይነ ምድር ነጻ በማድረግ ማስመረቅ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከውሃ ወለድና ከተላላፊ በሽታዎች ተጠቂነት በመከላከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡



