የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ሙራድ ከድር የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ ሾመ።

ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም

የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ሙራድ ከድር የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ ሾመ።

በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ ዙር 12ኛ አመት 8ኛ አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ሙራድ ከድር የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

በጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳደር እና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ አቅራቢነት አቶ ሙራድ ከድር በእጩነት ቀርበው የምክር ቤት አባሉ በሙሉ ድምፅ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ ሾሟል።

አቶ ሙራድ ከድር በጉራጌ በዞንና በወረዳ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በከፍተኛና በመካከለኛ የስራ ሀላፊነት ህዝብ ሲያገለግሉ የቆዩና በነበራቸው የስራ ቆይታ መልካም አፈፃፀም የነበራቸው ሲሆን በዛሬው እለት አቶ ሙራድ ከድር የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ተጠባባቂ ከንቲባ አድርጎ የምክር ቤት አባሉ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

አቶ ሙራድ ከድር ባደረጉት ንግግር ወልቂጤ ከተማ የብዙ ታሪኮችና የልማት እድሎች ባለቤት ፣ የታታሪዎችና የስራ ወዳዶች መፍለቂያ እንዲሁም የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖርያና የንግድ ኮሪደርና ከሀገራችን ከተለያዩ ክፍሎች የሚቀሳቀሱ እንግዶች ማረፊያ የሆነችው ከተማችን ካሏት ምቹ እድሎች አኳያ አቻ ከተሞች ከደረሱበት የእድገት ደረጃና ተወዳዳሪ እንድትሆን ሁሉም በቅንጅት ሊሰራና ሊያግዝ ይገባል ብለዋል።

በከተማዋ የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሰላምና የደህንነት ማስፈን፣ የህግ የበላይነት ማስከበር፣ የነቃ የማህበረሰብ የልማት ተሳትፎ በመፍጠር እና እኔነት ይልቅ እኛነት በማስቀደም ለከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ ሁሉም በጋራ መስራት መቻል አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።

በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ በተመሳሳይ አቶ ታደለ በቀለ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አድርጎ የሾመ ሲሆን ሹመቱም ለምክር ቤት አባላት ቀርቦ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

መረጃው የወልቂጤ ከተማ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ነው

3ኛ ዙር የአመራር የአቅም ግንባታ ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመከታተል ላይ የሚገኙ ሰልጣኞች በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የልማት ስራዎች ጉብኝት አካሂደዋል ።

የግብርና ምርትና ምርታማት በማሳደግና ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ አመራሩ በትጋት መስራት እንዳለበት ተገለፀ ።

3ኛ ዙር የአመራር የአቅም ግንባታ ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመከታተል ላይ የሚገኙ ሰልጣኞች በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የልማት ስራዎች ጉብኝት አካሂደዋል ።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ም/ሀላፊና በጉብኝቱ የቡድን አስተባባሪ አቶ መሀመድ ሙደሲር እንዳሉት ከጥቅምት 12/2017 ዓም ጀምሮ “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ በጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ሶስተኛ ዙር የአመራር የአቅም ግንባታ ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።

አመራሩ በስልጠና ያገኘውን ግንዛቤ በመጠቀም ለቀጣይ ተልዕኮ የላቀ ተነሳሽነት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር እንዲሁም በወንድማማችነትንና እህትማማችነት ዕሳቤ እንዲያጎለብት ይህ የልማት ስራ ጉብኝ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማት በማሳደግና ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲረጋገጥ አመራሩ በትጋት መስራት ግድ የሚልበት ወቆት ነው ያሉት አቶ መሀመድ በዛሬው እለት በእዣ ወረዳ የታዩት የልማት ስራዎች እጅግ የሚደነቁና ተስፋ የሚሰጡ ሲሆን በተለይም በፍራፍሬ እና በሰብል ልማት ስራዎች አመራሩ በተሞክሮነት በመውሰድ በየአካባቢው እንዲስፋፋ መስራት አለበትም ብለዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው ህዝብ በየደረጃው የሚያነሷቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው በመፈጸምና በማስፈጸም በተለይም ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል ዋንኛው የሆነው የግብርናው ዘርፍ ላይ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋልም ብለዋል።

እንደ እዣ ወረዳ አሁን ያለው የኑሮ ውድነትና የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ በመገንዘብ ሰፊ እንቅስቃሴዎች መደረጉን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ይህም ውጤታማ ለማድረግም በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን እና ከስነምህዳር ጋር የሚስማሙ የግብርና ምርቶች የበለጠ ተግባራዊ በማድረግ የአርሶ አደሩንና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል ።

በፍራፍሬ ልማት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ሲሆን በዓመታዊ ዋናና ዋና ሰብሎች ላይም ከሌላ አመታቶች በተሻለ ሁኔታ ለዘመናት ያልታረሱ መሬቶችን ጭምር እንዲታረሱ በማድረግ በአሁን ሰዓት በኩታገጠም በምርት በማሳ መሸፈናቸውንም የጠቆሙት አቶ ዘውዱ በኢንቨስትመንት ዘርፍም ዛሬ የጉብኝቱ አካል የሆነው ቲናው አበባ ልማትና ሌሎች በርካታ ኢንቨስትመንቶች ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና የልማት ስራዎችንም በማገዝ ውጤታማ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም በወረዳው በግብርናው ዘርፍ ሰፊ የሆኑ ለውጦች መኖራቸው እንደተመለከቱ ጠቁመው በተለይም በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ በየስራይ ቀበሌበጒፈ መንደር ውጤታማ የሆነው የፍራፍሬ መንደር ምስረታ የተመለከቱት እጅግ አስተማሪ ስራ በመሆኑ በተሞክሮነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ሌላው በወረዳው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉት እንቅስቃሴዎች እጅግ መነቃቃቶች ያሉ ሲሆን በተለይም በዛሬው እለት በጉብኝታቸው የተመለከቱት የበርካታ ስራአጥ ዜጎች ስራ የፈጠረው የቲናው አበባ ልማት እንቅስቃሴ አሰራሩ ኢንቨስትመንቱ በሚፈልገው ልክ በመሆኑ ለሌሎች አስተማሪ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በጉብኝቱ ወቅት የወረዳው መንግስት እና ጉብኝት ያደረጉባቸው ቀበሌ የሚገኙ አርሶአደሮች ስላደረጉላቸው መልካም አቀባበል አመስግነዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

“የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት”

3ኛ ዙር የአመራር የአቅም ግንባታ ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመከታተል ላይ የሚገኙ ሰልጣኞች በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የልማስራዎች እየጎበኙ ይገኛሉ ።

ከጥቅምት 12/2017 ዓም ጀምሮ “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ በጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ሶስተኛ ዙር የአመራር የአቅም ግንባታ ስልጠና በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው ።

ከጉራጌ ዞን የተወጣጡ ከ150 በላይ የመንግሥት አመራሮች በዛሬው እለት በእዣ ወረዳ ቲናው አበባ ልማት ፡ ሸህረሞ ቀበሌ ኩታ ገጠም የለማው የጤፍ ማሳ እና በየስራ ቀበሌ የፍራፍሬ መንደር የሆነው የጒፈ የልማት ቡድን የአቮካዶ ልማት እየጎበኙ ይገኛሉ።

በጉብኝት መርሃ ግብሩ ላይ የዞንና የወረዳው መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ዝርዝሩን ተከታትለን እናደርሳለን!!

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው

እያደገ ለመጣው የህዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በንቅናቄ መድረኩ በሰጡት የስራ መመሪያ እንደገለጹት እያደገ ለመጣው የህዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ይገባል ብለዋል።

ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ከችግር ለመውጣት በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የሚሰበሰበውን ገቢ በተገቢው መንገድ እንዲሰበሰብ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አመራሩ በገቢ አሰባሰብ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳደግ ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።።

አዳዲስ ሀሳቦችን እና አሰራሮችን መዘርጋት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የገቢ መሰረትን ማዘመን ተገቢ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ገቢን አሟጦ መጠቀም እና መሰብሰብ የፋይናንስ ዘርፉን ስኬታማ እንደሚያደርገውም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

ከተለያዩ መንገዶች የሚገኘውን ገንዘብ መቆጠብ እና ሀብትን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አሰራርን በማዘመን የሀብት ብክነትን መከላከል እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም በየደረጃው የሚገኘው አመራር የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

እያንዳንዱ መዋቅር እራሱን መቻል አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ገቢን መሰብሰብ፣ወጪን መቆጠብ፣ብክነትን ማስወገድ፣ቅንጅት እና ጠንካራ አመራር መስጠት ይገባል ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ እንደገለጹት በቀጣይ ሶስት ዓመታት ከእዳ ነጻ የሆነ ክልል ለመገንባት ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በግል እና በተቋማዊ አውድ ለውሳኔ አሰጣጥ፣ለእቅድ እና ስትራቴጂ ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር መሀመድ ጠቁመዋል።

የፋይናንሻል መረጋጋትን እድገት እና ዘላቂነትን ለማምጣት መሰረታዊ መርሆዎች እና አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ስለመሆኑ የተናገሩት ኃላፊው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመጣው የኢኮኖሚ ከባቢ ላይ ያለውን አበርክቶም አብራርተዋል።

የፋይናንስ ቢሮ ባሳለፍነው አመት የክልሉን መንግስት በጀት ዝግጅት እና የአስተዳደር ስርዓት በማጠናከር ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፣አመዳደብ እና የበጀት አጠቃቀምን ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኑን ዶ/ር መሐመድ በአብነት ጠቅሰዋል።

የመንግስት ሂሳብ አያያዝ እና ሪፖርት ላይ ከወቅታዊነት እና ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች መስተዋላቸውን የተናገሩት ኃላፊው በ2016 ዓም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በህግ በተቀመጠው አግባብ ብቻ ሀብትን በቁጠባ የመጠቀም ባህልን በማዳበር ወጪን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራም ዶ/ር መሐመድ አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም እንደገለጹት በ2016 በጀት አመት በፋይናንስ ሴክተሩ ያጋጠሙ ችግሮችን በመሻገር የመንግስት ተቋማት በተሟላ መንገድ ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን ጠቁመዋል።

በሁለት ዙር የመቶ ቀናት እቅድ በማዘጋጀት መደበኛ ስራዎችን ለመምራት ጥረት መደረጉን የተናገሩት ወ/ሮ ዘይቱና ከዚህ ቀደም የነበሩ እዳዎችን በማስተዳደር ረገድ የተከናወኑ ስራዎችን ኃላፊዋ በንግግራቸው ጠቅሰዋ።

የክልሉ መንግስት የነበሩ እዳዎችን ወደ ምንዳ ለማሸጋገር ጠንካራ የፖለቲካ አመራር ስርዓት በመዘርጋት የላቀ ድጋፍ ማድረጉን ኃላፊዋ አስረድተዋል።

ሴክተሩ በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣን እና ተግባር በአግባቡ ለማስፈጸም እንዲሁም የሀብት አስተዳደር ስርዓቱ ቀልጣፋ፣ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ወ/ሮ ዘይቱና ጠቁመዋል።

መረጃው የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ነው።

የመጌቻ መስኖ ፕሮጀክት በዘንድሮ ዓመት ወደ ልማት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ።

የመጌቻ መስኖ ፕሮጀክት በዘንድሮ ዓመት ወደ ልማት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ።

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ አጓይተረህና ከፊል ሸህረሞ ቀበሌዎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚችለው በመጌቻ ወንዝ ላይ መሰረት ያደረገው ይህ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የመጀመሪያ የግንባታው ደረጃ ሲጠናቀቅ 50 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚችል ተጠቁሟል ።

2.6 ኪ ሜትር እርቀት የሚሸፍነው የመጌቻ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ተገንብቶ ሳይጠናቀቅ ለብዙ አመታት በመቆየቱ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱ የሚታወስ ነው ።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተጀምሮ ድርጅቱ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተረክቦ በጀት ተመድቦ ስራዎች ቢሰራም ፕሮጀክቱን ግን ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ከማድረግ ጋር ጥቂት ለማይባሉ አመታት መጓተቱን ይታወቃል።

የእዣ ወረዳው መንግስት ይህንን በመገንዘብ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በቻለው አቅም አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ በዘንድሮ ዓመት ወደ ልማት በማስገባት አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል።

በዛሬው እለት የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ ፡ የእዣ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተሾመ ስራኒ ፡ የእዣ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ የርዮተአለም ዘርፍ ሀላፊ አቶ አብድህማን ሀሰን እንዲሁም የሚመለከታቸው የወዳው ተቋማት ተወካዮች የስራ እንቅስቃሴ የተመለከቱ ሲሆን የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ በአጭር ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ተግባር በሚገባበት ዙሪያ ላይ ከአካባቢው የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል ።

በወረዳው በ2017 ዓም በዋናና ደጋፊ መስኖ 1261 ሄክታር በማልማት 315 ሺህ 250 ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ መጣሉን የሚታወስ ነው።

በዞኑ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ጥቅምት15/2017ዓ.ም

========== በዞኑ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከልና ያሉትን ችግሮች ፈትቶ እንዲመጣ የተመደቡ ባለሙያዎች የድጋፍ ቡድን የደረሰበት ደረጃ ተገምግሟል፡፡

የድጋፍ ቡድኑ የሰራቸው ስራዎች፣ የወባ በሽታ ወረሽኝ ወቅታዊ ሁኔታና በቀጣይ ምን ምን ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ሰፊ ውይይት አካሄዷል።

በክትትልና ድጋፍ ወቅት ውስንነቶች የአጎበር አጠቃቀም ችግር፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች ማህበረሰቡ ባሳተፈ መልኩ አለመስራት፣ ጤና ኬላዎች ክፍት አድርጎ አገልግሎት ያለመስጠት ፣ የግብአት አቅርቦት ጉድለቶችን መኖራቸውን ተመልክተዋል።

በዚህም የቤት ለቤት የቁጥጥርና ግንዛቤ የማስጨበጥ በቀጣይ በልዩ ትኩረት መሰራት ይኖርበታል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ ከሐምሌ ወር ጀምሮ እየጨመረ የመጣውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የመቀነስ አዝማሚያ አልታየበትም።

በመሆኑም የወባ በሽታ ወረሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረጉ የድጋፍና ክትትልና የንቅናቄ ስራዎች እስከ ልማት ቡድን ድረስ በማጠናከር የመከላከሉ ስራ ማህበረሰቡ በባለቤትነት እንዲመራ ኃላፊነት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ የወባ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በልዩ ሁኔታ በመደገፍ ወረርሽኙ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በመጨረሻም የመምሪያው ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በየጊዜው እየጨመረ የሚመጣው የወባ ወረሽኝ በተገቢው ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ በማነቃነቅ ውሃ ያቆሩ አካባቢዎች በማዳፈንና በማፋሰስ፣ የአጎበር አጠቃቀምና ተያያዥ ጉዳዮች በዘመቻ መፈጸም ይገባል።

መረጃው የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ነው