




=======የጉራጌ አባቶች ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ ውጤት የሆነው ጀፎረ ከገጠር ኮሪደር ፕሮጀክት ጋር በማስተሳሰር ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።
ታህሳስ 17/2017 ዓ.ም
“ጀፎረ ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ” በሚል መሪ ቃል የገጠር ኮሪደር ለማልማት የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት የጉራጌ ጀፎረ የቀድሞ አባቶች ጠብቀው ለዘመናት ያቆዩትን ድንቅ እሴት መሆኑን ጠቅሰው ይህ እሴት ይዘቱን ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በቅንጅት መስራት ይገባል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ጀፎረ ከመጠበቅ ባለፈ የህብረተሰቡን የምግብ ስርአት ለማስተካከል ከሌማት ትሩፋት ጋር አስተሳስሮ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በየአካባቢው ቅርጻቸው እየተበላሸና እየጠበቡ ያሉ ጀፎረዎችን ከማስተካከል ባለፈ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ማስፋፋት ይገባል ነው ያሉት።
የገጠር ኮሪደር ልማት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንደሚሰራ የተናገሩት አስተዳዳሪው በቆርቆሮ የታጠሩ አጥሮችን በእንጨት አጥር መተካት ይገባል ያሉት አቶ ላጫ ሀገር በቀል የጥላ ዛፎች እንደሚተከልም ተናግረዋል።
የቀድሞ አባቶች ጠብቀው ያቆዩት የገጠር የምህንድስና ጥበብና እውቀት ምንጭ የሆነው ጀፎረ አመጣጥ ዙሪያ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የጉራጌ ምድር ጽዱ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ እንዲሆን እንደሚሰራ ገልጸው ይህም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኃላፊነቱ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በበኩላቸው የጉራጌ ዘመንን የቀደመ የምህንድስና ጥበብ አሻራ የሆነው ጀፎረ ባህሉና ይዘቱን ሳይለቅ ለማዘመን በገጠር ኮሪደር ልማት በማስተሳሰር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የጉራጌ አባቶች ጀፎረን ህግ አበጅተውለት ሲጠብቁት እንደነበር አንስተው ይህ እሴት ወደነበረበት በመመለስ በዘመናዊ መንገድ በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስተር በቅርቡ እንደ ሀገር ተግባራዊ የሚደረገው የገጠር ኮሪደር ልማት በዞኑ ሲሰራ በቆርቆሮ የታጠሩትን በእንጨት አጥርና በቀርከሀ በመቀየር መስራት እንደሚገባ ያነሱት አቶ አለማየሁ ለዚህም ውጤታማነት ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሰራም ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት ጀፎረ ለዘመናዊው የምህንድስና ጥበብ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ያነሱት ኃላፊዋ በዚህም ድንቅ እሴት የተለያዩ ማህበራዊ ኩነቶች የሚፈጸሙበት መሆኑን አውስተዋል።
በዞኑ ዘመናትን የተሻገረው ድንቅ የጥበብ አሻራ ጀፎረ ታሪኩንና ባህላዊ ይዘቱ ተጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም በአለም አቀፍ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ እና የባህል ተቋም ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ጀፎረ ባህላዊ ይዘቱን እንደተጠበቀ በአረንጓዴ፣ አገርበቀል ዛፎችና በፍራፍሬዎች ማስዋብ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ቱሪስቶች መዳረሻ እንዲሆን መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ ንጹህና ለኑሮ ተስማሚ በማድረግ ዘመናዊና ቀላል የአኗኗር ስልት እንዲከተል ከማድረጉ ባሻገር ለአርሶ አደሩ የተሻለ መሰረተ ልማት በመዘርጋት በገጠርና በከተማ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነትን የሚያጠብ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ከማህበራዊ ፋይዳው ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ጀፎረ የቀድሞ አባቶች ያለ ምህንድስና ጥበብ ለዘመናት ቢያቆዩትም የአሁኑ ትውልድ ይህ ድንቅ እሴት ከመንከባከብና ከመጠበቅ አንጻር ውስንነት መኖሩን አንስተዋል።
ታዲያ የቀድሞ አባቶች ያስቀመጡት አሻራ ተጠብቆ እንዲቆይ ከማድረግ ባለፈ የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቅሰው መንግስትም ስራው በሁሉም አካባቢ ውጤታማ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንዲሰራም ጠይቀዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።


















