






በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በቦዠባር ከተማ የሚኖሩ የሰባተኛ ቀን አዴቬንቲስት እምነት ተከታይ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነው የአምልኮና የቀብር ቦታ እና በከተማውና ዙሪያው ት/ቤቶች ለሚያገለግሉ በማህበራት ለተደራጁ መምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታ ርክብክብ ተደረገ ።
በርክብክብ ስነ -ስርዓቱ ወቅትም የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ እንዳሉት የወረዳው መንግስት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በከተማው የሚነሱ የተለያዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ከመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መካከል በቅርቡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነው የአምልኮና ቀብር ቦታ ምላሽ መሰጠቱን የገለፁት ዋና አስዳዳሪው በዛሬው እለትም በተመሳሳይ መልኩ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ ሳይሰጥ የቆዩት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት እምነት ተከታዮች የማምለኪያና ቀብር ቦታ እንዲሁም በቦዠባር ከተማ እና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚያገለግሉ መምህራን የመኖሪያ ቦታ መሰጠቱንም አስረድተዋል።
ይህም እንዲሳካ ከወረዳው መንግስት ጎን በመቆም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት የአካባቢው ነዋሪዎች: ከዞንና ከእዣ ወረዳ የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የሀይማኖት አባቶች ሚናቸው የጎላ ነበር ያሉት አቶ ዘውዱ በቀጣይም ሌሎችም የሚነሱት የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተያዘው መንገድ ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ የማህበረሰቡ ተሳትፎ የሚደነቅ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእዣ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ፅ /ቤት ሀላፊ አቶ ጌታቸው አየለ በበኩላቸው የቦዠባር ከተማ ሲመሰረት የተለያዩ እምነትና ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንደሚኖሩ ታሳቢ በማድረግ የከተማ ፕላን ሲሰራ የእምነት፣ የንግድ፣ የፋብሪካና የተለያዩ ተቋማት መስሪያ ቦታዎች ተመላክተው እንደሚቀመጡና ከነዋሪው የአምልኮ ቦታን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎች በሚቀርቡበት ጊዜ በከተማ መሬት አስተዳደር ስርዓት መሰረት ምላሽ እንዲሰጥ መንግስት የአሰራር ስርዓት በዘረጋው መሰረት የነዋሪው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የወረዳው መንግስት ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዛሬው እለትም የሰባተኛ ቀን አዴቬንቲስት እምነት ተከታይ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነው የአምልኮና የቀብር ቦታ ርክብክብ እና በከተማውና ዙሪያው ለሚገኙ በ4ማህበራት ለተደራጁ መምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የወረዳው መንግስት ከከተማው የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ሰፊ መግባባት በመፍጠር ርክብክብ መደረጉንም አስረድተዋል።
የከተማው ነዋሪ መሬቱ ሳያንገራግር በፈቃደኝነት ካሳ ተስጥቶት በመስጠትና መንገድ በራሱ ፍቃድ እንዲወጣ በማድረግ ያደረገው ርብርብ የሚደነቅ በመሆኑ አቶ ጌታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ያነጋገርናቸው የተለያዩ እምነት ተከታይ አባቶች በሰጡት አስተያየትም የከተማው ማህበረሰብ ከጥንት አባቶች ጅምሮ ሲወራረስ የመጣ የወንድም ህዝቦች በፍቅር የመኖር መገለጫ ሲሆን ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት እምነት ተከታዮች የአምልኮና የቀብር ቦታ መሰጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በከተማውና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚያገለግሉ መምህራን የጠየቁት በረጅም ጊዜ የመኖሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ በማግኘታቸውን መደሰታቸውን ተናግረዋል ።
በርክብክብ ስነ ስርዓቱ የወረዳው አመራሮች የኦርቶዶክስ ፡ የእስልምናና የሰባተኛ ቀን አድቪንቲስት እምነት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ,ቤት ነው።




