በየቀበሌ ያሉ ስራስኪያጆች በወረዳው ሞዴል በሆነው ሸብራደን ቀበሌ

========በየቀበሌ ያሉ ስራስኪያጆች በወረዳው ሞዴል በሆነው ሸብራደን ቀበሌ ላይ የወሰዱትን ተሞክሮ በተግባር በማዋል በመረጃ የተደራጀ ተቋምና በአገልግሎት አሰጣጥ የረካ ማህበረሰብ እንዲፈጠር የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለፀ ።

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም የገመገመ ሲሆን እንደ ወረዳው ሞዴል በሆነው ሸብራደን ቀበሌ ላይ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም አካሂዷል።

የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን ዘርጋ እንደገለፁት በየደጃው ያለው ፐብሊክ ሰርቫንት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱ በማሻሻል ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ስራአስኪያጆች የተጣለባቸው ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል።

በየቀበሌው የሚገኙ ስራአስኪያጆች የተሰጣቸው ሀላፊነት በአገልጋይነት ስሜት ለችግሮች ቶሎ መፍትሔ በማበጀት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለህብረተሰቡ በቅንነት እና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም ሀላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

እንደ ወረዳው ልምድ ሊቀስሙበት በማለም በዛሬው እለት ምልከታ የተደረገበት ሸብራደን ቀበሌ በወረዳ ተቋማት ደረጃ ጭምር ተሞክሮ የሚሆን ጠንካራና ግልፅ የመረጃ አደረጃጀት ስርዓት የታየበት ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ይህም በአግባቡ ከተሰራ ምንያክል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በቅጡ ተገንዝበው ስራአስኪያጆች በየቀበሌአቸው ተሞክሮውን ማስፋት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የእዣ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ፅ/ቤት ምክትል ሀላፊና የሪፎርም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጌትነት ወልዴ በበኩላቸው በየቀበሌው የሚገኙ ስራአስኪያጆች ተጠያቂነትና ሀላፊነት በሚሰማው መልኩ በአግባቡ በመስራት ራሳቸው ፡ ተቋማቸው እንዲሁም ወረዳቸው በአፈፃፀም ደረጃ ጥሩ እንዲሆኑ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

እንደ ወረዳው በየቀበሌው ጠንካራ ስራአስኪያጆች ለማብቃት በተለያየ መልኩ ስልጠና የመስጠት ፡ የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያመላከቱት ም/ ሀላፊው በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመትም በርካታ ጠንካራ ስራዎች መሰራታቸውንና በቀጣይም በጉድለት የተጠቀሱትን ቶሎ በማረም የማህበረሰቡ አገልግሎት አሰጣጥ ማሳደግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

እንደ ወረዳው በጥንካሬ ከሚጠቀሱ የቀበሌ ተቋማት መካከል የሸብራደን ቀበሌ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌትነት በዛሬውም የልምድ ልውውጡ ላይ የታዩት እጅግ አስተማሪና ጠንካራ የመርጃ አደረጃጀት ስርዓቶች በሁሉም ቀበሌዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በቂ ልምድ በመውሰድ ስራአስኪያጆች በየቀበሌያቸው ተሞክሮውን ተግባራዊ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየትም በሸብራደን ቀበሌ ያየነው እጅግ አስተማሪ የሆነ ተግባር እራሳችን የቱጋ መሆናችን እንድንፈትሽ የቤት ስራ የሰጠን አስተማሪ ተግባር በመሆኑ በቀጣይም መሰል የልምድ ልውውጥ መድረኮች መጠናከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም እንደየቀበሌያቸው በ6 ወሩ በአፈፃፀም ወቅት በጉድለት የተነሱትን በማረምና በጥንካሬ የተነሱትን በላቀ መልኩ አጠናክሮ በማስቀጠል ማህበረሰቡ ለማገልገል ተዘጋጅተናልም ብለዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ለኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጽ/ቤታቸው አቀባበል አደረጉ

=============ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ለኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጽ/ቤታቸው አቀባበል አደረጉ

የካቲት 23/2017 ዓ.ም

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ለተመራ ልኡክ በጽ/ቤታቸው አቀባበል አድርገዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ከልኡካን ቡድኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ተመስርቶ ወደ ተግባር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ክልሉ ሲመሰረት ከነባሩ ክልል የተላለፈ ከፍተኛ የእዳ ጫና እንደነበር የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ከ4 ነጥብ 8 እስከ 5 ቢሊየን ብር እዳ ስለመከፈሉ አብራርተዋል።

ምንም እንኳን ክልሉ በበርካታ የበጀት ጫናዎች ውስጥ ቢያልፍም በተለያዩ ከተሞች 7 የቢሮ ግንባታ ስራ መጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ርዕሰ መስተዳድሩ ለልኡካን ቡድኑ አብራርተዋል።

መንግስታዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ህንጻዎች በሁለት አመት ከስድስት ወራት ማጠናቀቅ የሚያስችል ግብ ተቀምጧል ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የተጓተተውን የወልቂጤ ሆስፒታል ለውጤት ማብቃት እንዲቻል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ትብብር ጠይቀዋል።

የጤና ስርዓትን ከማዘመን አንጻር የበለጸጉ ሶፍት ዌሮች እንደሚያስፈልጉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በክልሉ በርካታ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች መገንባታቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የህክምና ቁሳቁስ በማሟላት ረገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር )በአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት እንዲገነባ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በክልሉ 90 ፕሮጀክቶችን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

ፕሮጀክቶቹ 1ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚጠይቁ ሲሆን ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው በክልሉ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

ክልሉ በአጭር ጊዜ ተመስርቶ በፍጥነት ወደ ልማት መግባቱን ሚኒስትሯ አድንቀዋል።

የክልለን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የክልሉ መንግስት የወሰደው ቁርጠኛ አቋም የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በጤና ተቋማት ግንባታ፣በማህበረሰብ ጤና መድህን እና በሌሎችም የጤና ልማት ስራ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በየደረጃው ያለው መላው አመራር ለጤና ልማት ስራ በሰጠው ልዩ ትኩረት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በወልቂጤ ሆስፒታል ግንባታ ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ተጨማሪ ውይይት እና ጥናት እንደሚካሔድ አብራርተዋል።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። ዘገባው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነው።

የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው።

የካቲት 23/2017 ዓ.ም

የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው። የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ ዶ/ር

ሚንስትሯና ልዑካን ቡድናቸው በጉራጌ ዞን በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ምልከታ አድርገዋል።

የኢፌድሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው።

ሚኒስትሯ በወልቂጤ ጤና ጣቢያ የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ ፣የድህረ ወሊድ፣ የህክምና፣የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንዲሁም በጤና ጣቢያው በተለያዩ የስራ ክፍሎች እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ምልከታ አድርገዋል።

መንግስት በየደረጃው ህብረተሰቡን የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ መስሪያ ቤታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀ ይደረጋልም ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በጉመር ወረዳ የእንጀፎ መሰረታዊ ጤና ኬላ የአገልግሎት አሰጣጥና የሞዴል ቤተሰብ መንደር ምልከታ ያደረጉ ሲሆን በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውም አንስተዋል።

ፍትሃዊ የጤና ተቋማት ተደራሽ በማድረግ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ ለማፍራት በዘርፉ ይበልጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የወልቂጤ አጠቃላይ ሆስፒታል በክልሉ መንግስት ግንባታው መጀመሩን አንስተው ይህም ለብዙ ሆስፒታሎች ሞዴል የሚሆን በተለየ ስታንዳርድ እየተገነባ ነው ብለዋል።

ሆስፒታሉ በወቅቱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ በህብረተሰቡ ዘንድ በየጊዜው ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየተን አንስተዋል።

አጠቃላይ ሆስፒታሉ የህዝብና የመንግስት ሀብት ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው ለዚህም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለታለመለት አላማ እንዲውል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የህንጻው ተቋራጭ አቶ ዮሀንስ ሀይሌ የሆስፒታሉ ግንባታ የፊዚካል አፈጻጸሙ 86 ከመቶ መድረሱን አንስተው ይህም በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከድር መንግስት የህብረተሰቡን ጤና ለማበልጸግ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጥራት ለማሻሻልና ቀልጣፋና ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ የነበሩ ችግሮች ለመፍታት አዲስ የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ገብቷል።

በወረዳው በዘርፉ አበረታች ስራ መሰራቱንም ጠቁመው የተጀመረው አዲሱ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በጉመር ወረዳ አግኝተን ያነጋገርናቸው የእንጀፎ ቀበሌ ነዋሪዎች እንዳሉት የቤታቸው ንጽህና በመጠበቃቸው፣ ሽንት ቤት በየቤታቸው በመገንባታቸውና ቆሻሻ በተገቢው በማስወገዳቸው ጤንነታቸው እንደተጠበቀ አንስተዋል።

መሰረታዊ ጤና ኬላው በአቅራቢያቸው በመኖሩ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ትምህርት እንደሚሰጣቸውና ይህም ሁሉም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ተናግረዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው አመላክተዋል።

በመጨረሻም ለክብርት መቅደስ ዳባ ዶ/ርና ሉዑካን ቡድናቸው ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።