




ጥር 2/2018 ዓ.ም
============= በሳይንሱ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የፈጠራ ስራዎች ባለቤትነት መብት ማረጋገጥና ማበረታታት እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ጽ/ቤት ገለጸ።
ጽ/ቤቱ “የዘመነ ዲጅታል ኢኮኖሚ የዕድገታችን መሰረት ነው”በሚል መሪ ቃል በፈጠራ ስራና አዕምሮአዊ መብት ጥበቃ፣በኢትዮ ኮደርስ፣በኢኮቴ እቃዎች አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት በጉንችሬ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።
በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ ሐላፊ አቶ ደምስ ገብሬ እንደገለጹት ማናቸውም መንግስታዊና ህዝባዊ አገልግሎቶች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል በቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድ መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በሳይንሱ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የፈጠራ ስራዎች ባለቤትነት መብት ማረጋገጥና ማበረታታት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የእኖር ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ሐላፊ አቶ ምትኩ ሐይለማርያም ባለፉት ዘመናት ስንከተላቸው የነበሩ ሗላቀር አሰራሮችን በማዘመን ወቅቱ የሚጠይቀው በቴክኖሎጂ የታገዘና ጊዜ፣ጉልበትና ገንዘብ ቆጣቢ አገልግሎት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በየደረጃው ባሉት በትምህርት ቤቶችና በሌሎችም ተቋማት በከፍተኛ ወጪ የሚገዙ ኮምፒተሮች ፣ላፕቶፖችና ሌሎችም ለቴክኖሎጂው ተግባር አጋዥ የሆኑ ንብረቶችን በአግባቡ ልንገለገልባቸው ይገባል ብለዋል።
አክለውም ብልሽት የገጠማቸው ንብረቶችም ካሉ ህጉ በሚፈቅደው መንገድ በማስጠገን ለአገልግሎት እንዲበቁ በማድረግ ሁሉም የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የወረዳው ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ጽ/ቤት ሐላፊ ወ/ሮ ሙሉ ሻፊ በበኩላቸው በወረዳው በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በፈጠራ ስራ የበለጸገ ትውልድ በማፍራት ረገድ አይነተኛ ሚና አላቸውና ተልዕኮዋቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ጽ/ቤቱም የፈጠራ ስራ ባለቤቶችን መብት በማስከበር ረገድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ተቋሙ በተግባሩ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በቴክኖሎጂ የረቀቀ ትውልድ ለመፍጠር ጊዜውን የዋጀ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም ስልጠናው ለስራቸው ትልቅ አጋዥ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ከቴክኖሎጂው ጋር የተላመደ ትውልድ እንዲፈጠር የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በመድረኩም የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን፣የሳይንስ ክበባት ተጠሪዎች እና የተመረጡ የፈጠራ ስራ ባለቤቶች፣የወረዳው ሴክተር መስሪያ ቤት የልማት ዕቅድ ባለሙያዎች እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።









