=====እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ተግባራቶችን በማስቀጠልን ጉድለቶችን በማረም ማህበረሰቡ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።
የካቲት 6/2018 ዓም
በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 49ኛ መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል ።
የእዣ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሙከረም በደዊ ሃገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ሰው ተኮር ስራዎችን በመስራት ውጤቶች መመዝገባቸውንና እንደ ወረዳውም በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ተቋማት አቅደው እየሰራቸው የሚገኙ ስራዎች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
ይህ ጉባኤ ከሌላ ጊዜ ለየት የሚያደርገው የ2018 ዓም ሀገራዊ ምርጫ በሚካሄድበት ዋዜማ ወቅት መሆኑን የጠቆሙት ዋና አፈ ጉባኤው በመሆኑ በቀጣይ ምርጫውን የሚመጥኑ ስራዎች በመስራት ፍፁም ሰላማዊ እንዲሁን ከወዲሁ በትኩረት መስራት ይገባልም ብለዋል ።
በ2018 በጀት ዓም በመጀመሪያ ግማሽ አመት የተከናወኑ አበረታች ተግባራቶችን በማስቀጠልን ጉድለቶችን በማረም ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አቶ ሙከረም ጉባኤው ጨምረው ተናግረዋል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በ2018 ዓም ግማሽ ዓመት የተቋማት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱም በግብርናው ዘርፍ በ2017/18 ምርት ዘመን መኸር ወቅት በአዝዕርት ፡ በፍራፍሬና በሆልቲካልቸር ሰብሎች 10ሺ 408.2 ሄክታር መሬት በማልማት 987ሺህ 783.6 ኩንታል ምርት ለማልማት ግብ ተጠሎ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ እንደ ወረዳው ለዘመናት ያልታረሱ መሬቶች እንዲለሙ ሰፊ ጥረት የተደረገ ሲሆን በበልግ 1200 ሄክታር ፡ በመኸር 600 ሄክታር በድምሩ 1800 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ በእስካሁን ሂደት 1431.5 ሄክታር መታረሱንም ገልፀዋል።
1ሚሊየን 147ሺ የቡና ችግኝ የተተከሉ ሲሆን ፡ 118.5 ሄክታር የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ማልማት መቻሉን ፡ ከዝርያ ማሻሻያ አንፃር 1167 በመደበኛ ማደቀል አገልግሎት መከናወኑን የጠቆሙት አቶ ዘውዱ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት 14.5 ሄክታር በተለያዩ የሰብል አይነቶች መከናወኑና በመስኖና በሌሎችም የግብርና ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች መኖራቸውንም አብራርተዋል ።
በትምህርት ዘርፍ በ2017 ዓም የነበሩትን ጉለቶችን በማረም በ2018 ዓም የተለያዩ የውይይት ፡ የግንዛቤና የንቅናቄ ስራዎችን በማካሄድና የትምህርት አመራር ሪፎርም ስራዎች በመስራት በቅድመ መደበኛ 2687 : በጎልማሶች ትምህርት 5329 እንዲሁም በመደበኛ ትምህርት 14ሺ 388 ተማሪዎች በመመዝገብ የመማር ማስተማር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ በጀት ወሳኝ በመሆኑ በመንግስት ፡ በአጋር ድርጅቶችና በባለሀብቱና በማህበረሰቡ በድምሩ 29 ሚሊየን 61ሺህ ብር በመሰብሰብ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ ዘውዱ በትምህርት ዘመኑም ሁለት 2ኛ ደረጃ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች (ዳርቻ ዝግባቦቶ እና ይነቨረስ) የመማር ማስተማር ስራ መጀመራቸውንም ጠቁመዋል ።
በጤናው ዘርፍ በ6 ወሩ 1738 ያህል እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ በጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን 1749 ህፃናት የሳንባ መከላከያ ክትባት ፡ ለ1743 የፀረ-5 በሽታ ተከላካይ ክትባት ለ1655 ህፃናት የመጀመሪያ ዙር የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን በሪፖርቱ ያመላከቱት ዋና አስተዳዳሪ በዘርፊ ሌሎችም የተከናወኑ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም አመላክተዋል ።
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ወረዳው በሌሎችም ተቋማት የተከናወኑ በርካታ ስራዎች በሪፓርታቸው ያመላከቱት ዋና አስተዳዳሪው በምክር ቤቱ የተነሱት ለአብነትም በገቢ አሰባሰብ ፡ በስራ እድልፈጠራ ፡ በመስኖ ልማትና በመሳሰሉት ላይ በቀጣይ ትኩረት በመስጠት እንዲከናወኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበትም ብለዋል።
በእለቱም የእዣ ወረዳ ፍርድ ቤት የ6 ወር አፈፃፀም በፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት በአቶ ሙባሪክ ግርማ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በተቋሙ እየተከናወኑ የሚገኙ ጠንካራ ስራዎች ማስቀጠል እንደሚገባም የምክር ቤት አባላቱ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን በተጨማሪም የገቢ ምጣኔ ማሻሻያ አዋጅ ሰነድ ቀርቦ የምክር ቤት አባላት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
በእለቱም በምክር ቤት አባላቱ የተነሱት ጥያቄና አስተያየቶች በሚመለከታቸው ተቋማት ቀጣይ ለማረም እንዲቻል በየተቋማት አስፈፃሚ አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።