








የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን አሰራር ይፋ አደረገ።
30/06/2018 ዓ.ም አገና//
በዛሬው ዕለት የአገና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከማ/ኢ/ክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ቢሮ እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የተቋሙን የስልጠና ሂደት እና የአስተዳደራዊ ስራዎች ከወረቀት ንክክኪ ነፃ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ አስተዋውቋል።
ይህ ቴክኖሎጂ የሃብት እና የሰው ሀይል ብክነትን በመቀነስ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ፍጥነት በመጨመር ለክህሎት ልማቱ ዉጤታማነት ያለው ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ የታመነበት ነው።
የተማሪዎች ምዝገባን ጨምሮ ፈተና ማረም እንዲሁም የተማሪዎች ውጤት ሪፖርት ማድረግ የተቋሙን መማሪያ መፅሐፍት (ቤተ መፅሐፍት) በቀላሉ በስልክና በኮምፒውተር ማስጠቀም እንዲሁም ተመራቂ ተማሪዎች ባሉበት ሆነው ሰርትፊኬታቸውን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው እንዲደርሳቸው ማስቻል ቴክኖሎጂው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ይገኙበታል።
የማ/ኢ/ክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ቢሮ ም/ኃላፊ ኢንጅነር ሰለሞን ፈርሻ በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ እንደገለፁት ተቋሙ ተግባራዊ ያደረገው ይህ ቴክኖሎጂ በተቋሙ ዘንድ አስተዳደራዊና ተግባራዊ ቅልጥፍና እንዲሁም የተማከለ የመረጃ አስተዳደር እንዲኖር ያደርጋል።
ከዚህ በተጨማሪም የመረጃ ጥራት እንዲኖር ከማድረግ አኳያ እና ተቋሙ በእቅድ እንዲመራ
ከማድረግ አኳያ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ኢንጂነር ሰለሞን ጨምረው ገልፀዋል።
የአገና ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ከልል ክብሩ በበኩላቸው መንግስት የአሠራር ሥርዓቱን ለማዘመንና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ብልጽግና ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው የኮሌጁ አሰራር መዘመን ጠቀሜታው ለተቋሙ ብቻ ሳይሆን በከተማው ለሚገኙ ለሌሎች ተቋማት ሁሉ ተሞክሮ መቀመርያ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮምን ወክለው በስፍራው የተገኙት አቶ ዓለምነህ ታረቀኝ በበኩላቸዉ ተቋማቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ኢትዮ ቴሌኮም ከመንግሥት ጋር በመተባበር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት በአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተግባራዊ የተደረገው ተቋሙን የማዘመን ስራ በቀጣይ ወደ ሁሉም ኮሌጆች የማስፋት እቅድ መያዙንም ጨምረው ገልፀዋል።
የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አስቻለው ስባኒ በበኩላቸው ኮሌጁ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ያስጀመረው ይህ ቴክኖሎጂ ሀገራችን በ2030 ለማሳካት ያቀደችውን የዲጂታላይዜሽን ትግበራ አንድ አካል ነው ብለዋል።
የተቋሙን ጠቅላላ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል አለም ያሸጋግራል የተባለው ይህ ቴክኖሎጂ ባለቤትነቱ የኢትዮ_ቴሌኮም ሲሆን የተመረጡ ተቋማት በተመጣጣኝ ዋጋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተመቻቸው እድል የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆኑ ተገልጿል።
ዘገባው የአገና ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።



