







በዞኑ የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል ለቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው:- አቶ ላጫ ጋሩማ
ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም(ወልቂጤ) በጉራጌ ዞን አገና ከተማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በመንግስት ትብብር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው G+1 ደረጃውን የጠበቀ አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ተገኝተው በዞኑ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ መንግስት፣ ህብረተሰቡና አጋሮችን በማስተባበር በርካታ የትምህርት መሰረተ ልማት የማሻሻል ስራ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በዞኑ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከመንግስት ቀጥሎ ከትምህርት ስራ ባሻገር በጤና፣ በንጹህ መጠጥ፣ በግብርናና በሌሎችም አበረታች ስራ እየሰራችው መሆኑን ተናግረዋል።
ትናንሽ ልጆች እንደ ችግኝ ናቸው ያሉት አቶ ላጫ ለዚህም ልጆችን እንደችግኝ በተገቢው በመንከባከብ ከልጅነታቸው ጀምሮ ምቹ በሆነ ስፍራ በተገቢው ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
እንደ ሀገር የለውጡ መንግስት የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ቅድመ አንደኛ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዞኑም መንግስት ህብረተሰቡና አጋሮችን በማስተባበር ለቅድመ አንደኛ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዛሬው እለት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጥራትና በአጭር ጊዜ የተገነባው ደረጃውን የጠበቀ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ሞዴልና አርአያነት ያለው መሆኑን አንስተው ትምህርት ቤቱ መጠበቅና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ ፍቅሬ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኒቷ በዞኑ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በጤናና በሌሎችም በርካታ ስራዎች እየሰራች መሆኑን ጠቁመው ከዚህም ባለፈ በትምህርት ዘርፍ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በትኩረት በመስራት ላይ ናት ብለዋል።
በቀጣይም አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር መሰል ተግባራት ይበልጥ በማጠናከር ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ እንደምትሰራም ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በበኩላቸው እንደ ሀገር ብሎም በክልሉ ለትምህርት ጥራት ችግር በዋናነት የትምህርት ተቋማት ከደረጃ በታች መሆን፣ የመምህራን አቅርቦት፣ ብቃትና ተነሳሽነት ከፍተኛ ውስንነት እንደነበረበት አንስተዋል።
ለዚህም የስርአተ ትምህርት ለውጥ በማድረግና የሀገር የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ማሻሻልና የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ከተዘጋጀ ወዲህ የትምህርት ቤቶችን ደረጃና የመምህራን አቅም የማሻሻል፣ የትምህርት ቤት አመራር ሪፎርም የማድረግ፣ የተማሪዎች ምገባና የትምህርት ቁሳቁስ የማሟላትና ሌሎችም ስራዎች በመሰራቱ በዘርፉ ውጤቶች እየተመዘገበ ነው ያሉት።
በዛሬው እለት በከተማው ቤተክርስቲያኒቷ በርካታ ወጪ በማውጣት የተገነባው ደረጃውን የጠበቀ ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ለከተማና ለአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ፍይዳ እንዳለው አንስተው ይህም ህጻናቱ የነገ የህይወት መንገዳንና መዳረሻቸው እንዲወስን አብነት ይሆናል ብለዋል።
የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ መንግስት ህጻናት የሚማሩባቸውን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በከተማው በንጹህ መጠጥ ውሃ ስራዎች እየሰራች መሆኑን አንስተው በትምህርት ዘርፍም በዛሬው እለት በመንግስትና በቤተክርስቲያኒቷ ትብብር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ G+1 ደረጃውን የጠበቀ ባለ 8 የመማሪያ ክፍሎች፣ የመምህራን ቢሮ፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤትና ግብአት ያሟላ ትምህርት ቤት መገንባቱንም አመልክተዋል።
መረጃው የዞኑ መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ !!



