በፈጠራና በፍጥነት ታግዛ ወደ ማንሰራራት ከፍታ ስትጓዝ የመጣችበት ነው

ባለፉት ስምንት የለውጥ አመታት ኢትዮጵያ በአዳዲስ ሀሳቦችና ምናቦች በፈጠራና በፍጥነት ታግዛ ወደ ማንሰራራት ከፍታ ስትጓዝ የመጣችበት ነው:- ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሚያዝያ 13/2018ዓ.ም(ወልቂጤ) ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት እና ሰባተኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት በወልቂጤ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፍ ተካሒዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር (ዶ/ር) እንደሻው ጣሰው እንደገለጹት እንደ ሀገር መጋቢት 24 የተጀመረው የለውጥ ጉዞ አዳዲስ እርምጃዎችን በመጓዝና ልዩ ልዩ ስብራቶችን በማከም ውጤቶችን እንዲመዘገቡ አስችሏል።

በጠቅላይ ሚኒንስር ዶክተር አብይ አህመድ አርቆ የማሰብና አልቆ የመስራት ሀገራዊና ከባባዊ ጸጋዎችን በማስተዋልና በልማት ሀገርን የማሻገር የመሪነት ጥበብ የተመራ የስምንት ዓመት የለውጥ ጉዞ አዳዲስ እይታዎችን በመተለም ስብራቶችን በማከም ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ እያራመደ ይገኛል ብለዋል።

በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስኮች ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ታላላቅ የሪፎርም እርምጃዎችንም መወሰዳቸውም አመላክተዋል።

ከዚህም በላይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የተቃኙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራ በመደረጉ በዚህም አስደማሚ ውጤቶችን መመዝገባቸውንም ተናግረዋል።

በሀገሪቷ የፖለቲካ ስርአት ግንባታ ሂደት መሰረታዊ ችግር ሆኖ የቆየው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ስብራት እንዲጠገን የፍቅርና የይቅርታ መንፈስ ከፍ በማድረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ምህዳር ማስፋት መቻሉንም ጠቁመዋል።

አክለውም በንግግርና በምክክር ችግሮችን በመፍታት በትብብርና በፉክክር መንፈስ አብሮ ከመስራት አኳያ በርካተ የለውጥ እርምጃዎች ተወስደዋል፣ በዚህም ታላላቅ ውጤቶችም ተመዝግቧል ነው ያሉት።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ዘርፉ ብዙ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ያነሱት ዶ/ር እንዳሻው በዚህም በርካታ ለውጦች መመዝገቡንም አስረድተዋል።

በኢኮኖሚ መስክ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ መሰረት በማድረግ የየአካባቢው ጽጋዎችና ልዩ አቅሞችን በማናጀት እምርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን አውስተዋል።

በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሻሻል የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የምግብ ሉአላዊነት የተረጋገጠችበት ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ታላላቅ አሻራዎችን ማኖር ተችሏልም ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ፣ በቱሪዝም አማራጮችና በቴክኖሎጂ መስክ፣ ከተማና ከተሜነትን ለማዘመንና ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በመጨረስ፣ በማህበራዊ ዘርፍ፣ በዲፕሎማሲ ግንኙነትና በሌሎችም አስደናቂ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ መንግስት መሪነት በመደመር እሳቤ ቅኝት ባለፉት ስምንት የለውጥ አመታት ኢትዮጵያ በአዳዲስ አሳቦችና ምናቦች በቁጭት፣ በፈጠራና በፍጥነት ታግዛ ወደ ማንሰራራት ከፍታ እየተራመደች እንደምትገኝም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማንሰራራት ከፍታ ጉዞ ዳር ለማድረስ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም ሁሉም ዜጋ ከብልጽግና ፓርቲ ጎን እንዲቆምም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።