



የእዣ ወረዳ ምክር ቤት የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሞ የልማትና የአስተዳደር አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።
ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም (አገና)
የእዣ ወረዳ ምክር ቤት የ4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት 52ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ የወረዳውን የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም በዝርዝር ገምግሟል።
በጉባኤው የ26 ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች የተመረመሩ ሲሆን፣ የወረዳው የአስተዳደር ምክር ቤት ሪፖርት ከማጽደቅ ባለፈ አዳዲስ የሥራ ኃላፊዎችና አመራሮች ሹመትንም በይፋ አጽድቋል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የእዣ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ሙከረም በደዊ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ አዎንታዊ ሥራዎችን በማከናወን ከፍተኛ ውጤቶችን እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
አያይዘውም በወረዳው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበው፣ በጉባኤው የሚቀርቡ ሪፖርቶችን በንቃትና በኃላፊነት ስሜት በመወያየት የተላለፉ ውሳኔዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ሁሉም አካላት በትጋት እንደሚረባረቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ የወረዳውን የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ ናቸው።
በሪፖርታቸውም የመረጃ ክፍተቶችን ማረም፣ ሥራዎችን በባለቤትነትና በትኩረት ማከናወን ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። እንዲሁም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በተቀናጀና በተሳሰረ መንገድ ማከናወን ለዘላቂ ውጤት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በወረዳው ሥር የሚገኙትን 26 ተቋማት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች በዝርዝር የገመገመ ሲሆን፣ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ከሕብረተሰቡ ተሳትፎ ጋር የውኃ ሥራዎችን ለማከናወን 1.5 ሚሊዮን ብር ታቅዶ 1.2 ሚሊዮን ብር በማከናወን 80 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል። በተጨማሪም በገጠር የመጠጥ ውኃ አገልግሎት ማጠናከር፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥናትና የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።
የትራንስፖርትና መንገድ አንፃር RR10 ደረጃ ያለውን የአፈር ስራ መንገድ ጥናትና ዲዛይን 13 ኪሎ ሜትር ለማከናወን ታቅዶ 12.4 ኪሎ ሜትር ተከናውኗል።
የተሽከርካሪዎች ፍተሻና ደህንነት ክትትል አንፃርም ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በተወሰደ የፍተሻ እርምጃ 271 ሕገወጥ አሽከርካሪዎችን በመያዝ 331,200 ብር ቅጣት ለወረዳው ገቢ ማድረግ ተችሏል።
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የሴቶች ልማት ማኅበራትን በማደራጀትና ድጋፍ በማድረግ ረገድ 106 ታቅዶ 78ቱንም ማከናወን መቻሉን የተገለፀ ሲሆን አቅም ለሌላቸው ሴቶችና ሕፃናት የተለያዩ ማኅበራዊ ድጋፎች ተደርገዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተም የሥራ አጥ ልየታ 5,294 ታቅዶ 5,364 በማከናወን 101.3 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል። ከብድር ማሰራጨትና ማስመለስ ጋር በተያያዘም 69.76 በመቶ ማስመለስ መቻሉን በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በትምህርት ዘርፍ የቅድመ አንደኛና የመደበኛ ትምህርት ተማሪዎች ምዝገባ በጥሩ ሁኔታ መከናወኑ የተገለፀ ሲሆን በጤና ዘርፍም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት 99.8 በመቶ፣ የቅድመ ወሊድ ክትትል ደግሞ ከ97 በመቶ በላይ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
በመኸር ልማት 95 በመቶ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ 13.17 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል 98 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
የወረዳው ምክር ቤት የ26ቱን ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች ከመረመረና የተመዘገቡ ጥንካሬዎችንና ያሉ ክፍተቶችን ከገመገመ በኋላ፣ የወረዳውን የአስተዳደር ምክር ቤት የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት አጽድቋል።
ምክርቤቱ በተጨማሪም አዲስ የተመደቡ የሥራ ኃላፊዎችና አመራሮች ሹመትን መርምሮ አፅድቋል
ጉባኤው በቀጣይ በመሠረተ ልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎች የልማት ዘርፎች የሚታዩ ክፍተቶችን በትኩረት በመለየትና በመፍታት፣ የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።




