
===================================
ጥቅምት 17/2016 ዓም
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት ተማሪዎች የማህበረሰቡ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት ገለፀ ።
የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት እና የወረዳው ትምህርት ፅ/ቤት በጋራ የተዘጋጀ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ድጋፍ ክትትል አቅም ግምባታ ፡ የ2015 ዓም አፈፃፀም እና የ2016 ዓም ማጠናከሪያ ፡ በሳይንስ ክበባት እንዲሁም በአእምሮ ንብረት ጥበቃ ዙሪያ ለባለ ድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል ።
በእለቱም የእዣ ወረዳ ም/ አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለፁት ቴክኖሎጂን በመዘርጋትና በማስፋፋት በህብረተሰቡ ውስጥ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ማጥበብ ያስፈልጋል ።
ለዚህም ትልቅ እድል ሚፈጥረው በትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻሉባቸው በቂና ምቹ የሆነ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባም ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል ።
የፈጠራ ስራዎችን በትምህርት ቤት ደረጃ በስፋት እንዲተገበሩ መደገፍና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተጠምቀ በተቋማት በዘርፉ እየተስተዋለ ያለውን የግብዓትና ሌሎችም ክፍተቶች ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመላክተዋል ።
የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሪት ራሂማ ሙክታጅ በበኩላቸው በቀጣይ ለሚደረገው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤግዚብሽን ውድድር ላይ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪውች የፈጠራ ስራቸው ከወዲሁ እንዲያዘጋጁና ከወረዳው አልፎ በዘርፉ በሚኖሩ ኤግዚብሽንና የባዛር ውድድሮች እንዲሳተፉ በማቀድ ከአሁኑ የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የፈጠራ ስራዎችን በትምህርት ቤት ደረጃ በስፋት እንዲተገበሩ ፅ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ሀላፊዋ በተለይም በትምህርት ቤቶች የተለያዩ ፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ተማሪዎችን በማበረታታት ሀገራችን ኢትዮጵያ በተክኖሎጂ ዘርፍ ውጤታማ እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጨምረው ገልፀዋል ።
በጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የፈጠራ ስራዎች ድጋፍ ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሮክቴሬት ዳይሬክተር ታሪኩ ንዳ እንደገለፁት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሁሉለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ በመገንዘብ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ለማሳደግ በተለይም የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ሀላፊነት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት ተማሪዎች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ የወረዳው ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅ/ቤት እየሰራ ያለው ተግባራት ለሌሎችም ተሞክሮም ጭምር የሚችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየትም ተቋሙ እያደረገው ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው አሁንም እስከ ትምህርት ተቋማት ድረስ በመውረድ እያከናወነው ያለው ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል ።
በእለቱም በተቋሙ በ2015ዓም በጀት ዓም ጥሩ አፈፃፀም ያላቸው ከ1- 3 የወጡ ባለሙያዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።






©2023. የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ከአገና ኮንስትራክሽን እና ኢደስትሪያል ኮሌጅ ጋር በመተባበር. All Rights Reserved.