በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የቆጠር ገድራ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤት ተማሪዎችና መምህራን 40 ዩኒት ደም መለገሳቸው ተገለፀ ።
የደም ልገሳ ፕሮግራሙ በእዣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት አስተባባሪነት የተካሄደ ሲሆን የፅ/ቤቱ ሀላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ እንደገለፁት በወሊድና በተለያዩ የጤና ችግሮች ምክንያት እናቶችና ህፃናት ብሎም ወገኖቻችን በደም እጦት ምክንያት ውድ የሆነው ህይወታቸውን ለመታደግ ሁሉም ህብረተሰብ ደም በመለገስ የወገን ደራሽ ወገን እንደሆነ በተግባር ማረጋገጥ አለበት ብለዋል ።
በመሆኑ በወረዳውም በተለያዩ ጊዜያቶች ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ሁኔታው ልምድ እየሆነ መምጣቱ ለሌሎች አካባቢዎች ምርጥ ተሞክሮ እንደሆነ የጠቀሱት ሀላፊው በዚህ ፕሮግራምም በቆጠር ገድራ 2ኛ እና መሰናዶ ት/ቤት የሚገኙት መምህራንና ተማሪዎች በዚህ የደም ልገሳ ፕሮግራም 40 ዩኒት ደም መለገሳቸውን ገልፀዋል።
ይህም በጎ ተግባር በቀጣይም በማጠናከር በተለያየ ምክንያት ይጠፋ የነበረውን ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት በመታደግ መላው ህብረተሰብ ደም የመለገስ ልምዱ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ መሀመድ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
በደም ልገሳው ፕሮግራም የተሳተፉት ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ደም በመለገሳቸው የህሊና እርካታ እንዳስገኘላቸውና ቀጣይም መሰል የበጎ አድራጎት ስራቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።