የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

=================

” ውሳቻ ”
የጉራጌ ማህበረሰብ እንደሌሎቹ የሀገራችን ብሄረሰቦች የራሱ የሆኑ የተለያዩ ባህላዊ እሴት ባለቤት ነው፡፡

እነዚህ ባህለዊ እሴቶች የሚከወኑት በማህበረሰቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ሲከወኑ ይስተዋላል ከነዚህ የእርስ በርስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን ከሚያዳብሩ ባህላዊ እሴት አንዱ ውሳቻ ተጠቃሽ ነው::

ውሳቻ የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም የእንሰት አዝመራ ወይም የእንሰት ምርቶች የሚሰበሰብበት ወቅት ሲሆን የጉራጌ እናቶች በየአካባቢያቸው አንድ ላይ ሆነው
እንሰት የሚፍቁበት የደቦ ስርአት “ውሳቻ” ተብሎ ይጠራል፡፡

ውሳቻ የሚጀምረው በብሄረሰቡ የዘመን አቆጣጠር መሸ ወይም ጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ ባለው ነው፡፡

ይህ ሲባል ሁሉም አካባቢ በተመሳሳይ ወቅት ይጀምራል ለማለት አያስችልም ለምሳሌ የደጋው አካባቢ ከወይና ደጋ አካባቢዎች አስቀድመው እንደ ሚጀምሩ የማህበረሰቡ እናቶች ያሰረዳሉ ።

ውሳቻ ከሌሎች ለየት የሚያደረገው አቅም የሌላቸው እናቶች መስራት አትችሉም ተብለው ማግለል ሳይሆን የቻሉትን ያህል ተሳታፊ ሆነው የእንሰት ምርታቸውን መሰብሰብ መቻላቸውና አቅመ ደካሞችን የነፃ ጉልበት እርዳታ ማድረጋቸው ውሳቻን ልዩ ያደርገዋል።

እንዲሁም በአካባቢ ለቅሶ ከተከሰተ የለቀስተኛው ቤት አንድ ዙር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የእንሰት ምርት እንዲሰበሰብ ይደረጋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ሲገጥሙ የመረዳዳት ባህላዊ እሴቶች ጎልቶ ይታያል።
ይህ ውብ ባህላዊ እሴት ሲከወን የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች ይዜማሉ ከነዚህም ውስጥ ዋይ ወቶ ተጠቃሽ ነው ።