










===================================================================
#በውብ_እጆች_የተሰሩ_የዕደ_ጥበብ_ውጤቶች
➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳➳
የጉራጌ ማህበረሰብ የሠው ልጅ ተፈጥሮን ለእርሱ በሚመቸው አይነት መልኩ መግራት ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ተፈጥሮ የቸረችውን ከአካባቢው የሚገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም ለየዕለት ህይወቱ አስፈላጊ የሆኑትን ቁሶች ከማምረት ባሻገር ለረዥም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ መገልገያዎችን ጭምር በመስራት ዕውቀቱን ለትውልድ አሸጋግሯል፡፡ እያሸጋገረም ይገኛል፡፡
ከእነዚህ የጉራጌ መለያ ናቸው የሚባሉት የዕደ-ጥበብ ውጤቶች መካከል ጥቂቶቹን ለአብነት እንኳ ብንጠቅስ እንደ የብረት፣ የሸክላ፣ የእንጨት፣ የቀንድ፣ የሽመና፣ የቆዳ፣ የቃጫ፣ የስንደዶ እና የቄጠማ ስራዎች እናገኛለን፡፡
የማኅበረሰቡ ዕውቀትና ክህሎት አሻራ በእነዚህ የዕደ-ጥበብ ዘርፎች አርፎባቸዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ በጉራጌ ዞን በሚገኙት አንዳንድ ወረዳዎች ከስንደዶ፣ ከአክርማ፣ ከቃጫና ክር የሚመረቱ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ከአካባቢውና ከአገር አልፈው ከባህር ማዶም ባሉት ገበያዎች ላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡
ከነዚህ ውብ የእደ ጥበብ ውጤቶች መካከል ጥቂቶቹ፡-
1. #ይወደረ
በእንሰት አብቃይነቱ የሚታወቀው የጉራጌ ብሔር እንሰትን ከምግብነት በተጨማሪ ለተለያዩ ግልጋሎቶች ይጠቀሙበታል፡፡ ከነዚህም ለምግብ ማዘጋጃነትና ማቅረቢያነት፣ ለመኝታና ለቤት ውስጥ ንጣፍነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይወደረ ለምግብ ማቅረቢያነት የሚያገለግል ሲሆን የሚሰራውም የእንሰት ውጤት በሆነው በቃጫ ነው፡፡ ይህም ውበት እንዲኖረው በተለያየ ቀለማት ይነከራል፡፡ አንድ ጥሩ የተባለ ይወደረ ሰርቶ ለማውጣት እስከ አንድ ወር ጊዜ
የሚፈጅ ሲሆን እንዲህ አይነቱ ይወደረ ቁመቱ ሁለት ሜትር፣ ጎኑ[ስፋቱ] ደግሞ አንድ ሜትር ያህል ይሆናል፡፡
ይወደረ በተለይ ትላልቅ ክብረ-በዓላትና ትላልቅ ዝግጅቶች ሲኖሩ ቤት ውስጥ ወለል ላይ በተነጠፈ ሰፊና ምርጥ ጅፐ [ጅባ] ላይ ይዘረጋና ቆጮ፣ ክትፎ፣ አይብና የጎመን ክትፎ በጣባ ወይም በጥለስ [ከእንሰት ቅጠል የተሰራ ለመመገቢያነት የሚያገለግል] እንዲበላበት ለታዳሚው ይዘረጋል፡፡ በተለይ በመስቀል ወይም በአረፋ ክብረ በአላት ጊዜ ይወደረ እንዳይቆሽሽ ተጠቅልሎ በንጽህና ከተቀመጠበት ቦታ ይወጣና እስከ በዓላቱ ፍፃሜ ድረስ
ጅፐ ላይ ተዘርግቶ ማዕድ ማቅረቢያ ሆኖ ሲያገለግል ይቆያል፡፡
2. #ጅፐ [ጅባ]
ሌላው ከእንሰት ተክል እና ከቄጠማ የሚሰራው የዕደ-ጥበብ ውጤት ጅፐ [ጅባ] ይባላል፡፡
ይህ የዕደ-ጥበብ ውጤት ከእንሰት ተክል ከሚገኘው ቃጫና ኮባ የሚሰራ ሲሆን ለቤት ውስጥ ወለል ንጣፍነትና ለመኝታ አገልግሎት ይውላል፡፡
የተለያየ መጠንና ጥራት ያላቸው የጅፐ አይነቶች ሲኖሩ በጣም ምርጥ የተባሉት ልክ እንደ ይወደረ ለተለያዩ ክብረ-በዓላትና ለትላልቅ ዝግጅቶች ብቻ ግልጋሎት
የሚሰጡ ናቸው፡፡
መሃከለኛ የሆኑት ደግሞ ዘወትር ተነጥፈው በህዝቡ የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
3. #ሰፍ [መሶብ]
ሰፍ [መሶብ] ከስንደዶና ከአክርማ የሚሰራ ሲሆን በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ የተለያየ ቅርፅና መጠን ያላቸው ሰፍ [መሶብ] እየተሰሩ ለተለያዩ የማዕድ አገልግሎቶች ሲውሉ ይስተዋላሉ፡፡
እነዚህ በልዩ ልዩ ህብረ-ቀለማት ያጌጡ ውብና ማራኪ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ከቡና ቁርስ ማቅረቢያነት እስከ እንጀራና ዳቦ ማስቀመጫነት ሲያገለግሉ ትላልቅ
ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም በዋናነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡
ልዩ ልዩ የሸክላ ምርቶች በጉራጌ እጅግ መጠነ ሰፊ ግልጋሎት የሚሰጡ የሸክላ ስራ ውጤቶች ይሰራሉ፡፡
እነዚህ የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ለምግብ ማብሰያነትና ማቅረቢያነት፣ ለመጠጫነት፣ እንዲሁም የሚበሉና የሚጠጡ ምግቦችና መጠጦችን ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ ማቆያነት [ማስቀመጫነት] የሚጠቀሙበት ሲሆን አንዳንዶቹም
ከአንድ በላይ ለሆነ ጠቀሜታ ይውላሉ፡፡
እንደ ጀበና፣ የክትፎ አይብ ማቅረቢያና ማዋሃጃ ጣባ፣ ቅቤ ወይም ማር ወይም ወተት ማስቀመጫ፣ ጥዋ፣ የሸክላ ድስት፣ እንስራና ጋን ታዋቂ የብሔሩ የዕደ-
ጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡
4. #አንቀፎ [ማንኪያ]
ጉራጌ ከከብት ቀንድ የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን ይሰራል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋንኛው አንቀፎ [ማንኪያ] ነው፡፡
አንቀፎ የተለያየ መጠን ያለው ሲሆን አነስተኛው ለክትፎ፣ ለአይብ፣ ለዝማሙጃት፣ ለኸቋት፣ ለፍንታፍንቶ፣ ለኦዛት፣ ለድኩቸ እና ለማር ወለላ መመገቢያነት ሲያገለግል ትልቁ ደግሞ በትልቅ ጣባት ክትፎ፣ አይብ፣ ዝማሙጃት እና የጎመን ክትፎ ከቅቤና ሚጥሚጣ ጋር ለመለወስና ለማቀላቀል
ይጠቀሙበታል።
Visit Gurage






©2023. የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ከአገና ኮንስትራክሽን እና ኢደስትሪያል ኮሌጅ ጋር በመተባበር. All Rights Reserved.