






====በቀሪ ወራት የታቀዱ ተግባራትን በመፈፀም የተቋም አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ
ሆሳዕና፡ ታህሳስ 16/2018 ዓ.ም የሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ አካሄዷል።
በግምገማ መድረኩ የመምሪያው የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።
የሀዲያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሪት ገነት ሙሉጌታ እንደገለፁት መምሪያው ዘመኑ የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መድረኩ መዋቅሮች የተሰጣቸውን ተልዕኮዎች ከመፈፀም አንፃር ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ያለመ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊዋ ለዚህም መምሪያው ከጽ/ቤቶችና ዩኒቶች ጋር የዕቅድ ክንውን ግብ ስምምነት መግባቱን አስታውሰዋል።
ሁሉም ተቋማት የማህበረሰብ መረጃ ማዕከላትንና የቪዲዮ ኮንፍረንስ አዳራሾችን በማደራጀት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት አቅርቦቶችን ማሳደግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ኃላፊዋ አያይዘውም የአዕምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ዙሪያ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ሊታረሙ እንደሚገባ ጠቁመው ለዚህም በየአካባቢው የሚገኙ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶችን በማቀፍ ጠንካራ ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የመምሪያ ልማት ዕቅድ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ምትኩ ማኪሶ የአፈፃፀም ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ስራዎችን ማሳለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መምሪያው ለተለያዩ ተቋማት ሃርድዌርና ሶፍትዌርን በማልማት ውጤታማ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ያወሱት አቶ ምትኩ በዚህም በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ትምህርተ ቤቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ በየአካባቢያቸው የኤግዚቢሽን መርሃ-ግብር እንዲያዘጋጁ ተግባቦት በመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የገለፁት።
በበጀት ዓመቱ እንደ ሀገር የትኩረት መስክ የሆነውን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ለሁሉም የማህበረሰቡ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ የታቀደውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ግምገማው በተቋም አሰራር ወቅት የዕቅድና አፈፃፀም መጣረስ እንዳይስተዋል አመላካች የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች የተንፀባረቀበት መሆኑን አንስተዋል።
የግብዓት አቅርቦት እና የኔትዎርክ ዝርጋታ ስራዎችን ለማሳለጥ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮች በመሆናቸው መምሪያ ከሚመለከተው አካል ጋር ትኩረት በመስጠትና በመቀናጀት መቅረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም መምሪያው ስራ ለማቀላጠፍ ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በድጋፍ የተገኙ ቁሳቁሶችን ለሁሉም መዋቅሮች አበርክቷል።
በግምገማው የሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የከተማ ዩኒት አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።







