




=====በጤና መድን የተሻለ ነገን እንገንባ! በሚል መሪ ቃል በእዣ ወረዳ የ2019 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ
ህዳር 8 ቀን 2019 ዓ.ም (አገና)
በእዣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት “በጤና መድን የተሻለ ነገን እንገንባ!” በሚል መሪ ቃል የ2018 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን (ማዐጤመ) ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የንቅናቄ መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለጹት፣ የጤና መድን ሥርዓትን በአገራችን ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛ ዓላማው የጤና አገልግሎት ወጪ በማኅበረሰቡ ላይ የሚያስከትለውን የገንዘብ ጫና መቀነስ፣ ፍትሐዊና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማጎልበትና ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ማረጋገጥ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ተጠምቀ አክለውም፣ የማዐጤመ አገልግሎት የሚያካትታቸውን የአገልግሎት ዘርፎች በአግባቡ መለየትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ መያዝ እንዳለባቸው ገልፀው የማዐጤመ አገልግሎት የካርድ ክፍያን፣ የባለሙያ (የምርመራ) ክፍያን፣ የላብራቶሪ ክፍያን፣ የዲያግኖስቲክ ክፍያንና የመድኃኒት ክፍያን የሚያካትት ማዕቀፍ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በዜጎች መካከል ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ መላውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ከጤና መድን ተጠቃሚ እንዲሆን የተለዩ ጉድለቶችን በፍጥነት በማረምና በቅንጅት በመሥራት ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የእዣ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሰይድ በበኩላቸው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የመደጋገፍ ባህል በማጠናከር ፍትሐዊ፣ ጥራት ያለውና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ አካል መሆኑን ገልፀው ይህም ጤንነቱ የተጠበቀና ለምርታማነት የሚበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ መሐመድ አክለውም፣ ባለፉት ዓመታት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሥርዓትን በወረዳው ለማስፋፋት ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱንና በዚህም የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማሻሻል አንጻር የሚታይ ውጤት መመዝገብ መጀመሩን ገልጸዋል።
በወረዳው የሚገኙ 24 ቀበሌዎችን በአራት ክላስተሮች በማደራጀት የማዐጤመ እንቅስቃሴን በማጠናከር የጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም የገለፁት አቶ መሀመድ የ2019 በጀት ዓመት የማዐጤመ ንቅናቄ መድረክ መካሄዱ፣ በ2018 በጀት ዓመት የታዩ ጠንካራ ጎኖችንና የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ የተሻለና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
በመድረኩም የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በጉባኤው የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ፣ የእዣ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ ሙከረም በደዊን ጨምሮ የወረዳው ካቢኔ አባላት፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፣ ርዕሰ መምህራንና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።
See less






