


=====በእዣ ወረዳ ለንግዱ ማህበረሰብ በሕጋዊ የንግድ አሠራርና በሸማቾች ጥበቃ ዙሪያ የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ቀጥሏል።
ህዳር 09/2019 ዓ.ም(አገና)
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የንግድ ማህበረሰቡ ሕጋዊና ፍትሐዊ የንግድ አሠራርን እንዲከተል ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በዳርቻ ዝግባቦቶ ከተማ ተካሂዷል።
ሥልጠናው በወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት አማካኝነት ለንግዱ ማህበረሰብ አባላት እየተሰጠ ሲሆን፣ በንግድ ሕጋዊነት፣ በገበያ ቁጥጥርና በሸማቾች መብት ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጓል።
በመድረኩ የተገኙት የወረዳው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ሙሉጌታ፣ ነጋዴዎች ስለሚኖራቸው መብትና ግዴታ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ሕጋዊ የንግድ አሠራርን እንዲከተሉ የክህሎትና የእውቀት ክፍተቶችን መሙላት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም አዳዲስ መመሪያዎችና የንግድ ሥርዓት ማሻሻያዎች ወደ ተግባር ከመግባታቸው በፊት ለነጋዴው ማህበረሰብ ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ይድነቃቸው አክለውም የከተሞችን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ያለውን ሚና በማንሳት፣ ሕጋዊ ነጋዴዎች ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል ለአካባቢው ልማት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ነጋዴዎች ሕግና ደንብን በማክበር ከመሥራት ባለፈ፣ ሕገወጥ ንግድንና ደላላነትን በመታገል የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል። በተጨማሪም የመለኪያ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ ሁሉም ነጋዴ ዲጂታል ሚዛን እንዲጠቀም አመልክተዋል።
በንግድ ተቋማት ውስጥ ወቅታዊ የዋጋ ዝርዝርና የታደሰ የንግድ ፈቃድ በግልጽ ቦታ ማሳየት የግድ መሆኑንም አስታውሰው፣ ያለበቂ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በገበያ ውስጥ ፍትሐዊ ውድድርንና የሸማቾችን መብት የሚጎዱ ተግባራት ላይም ትኩረት ተሰጥቷል። ከእነዚህም መካከል ምርቶችን ደባልቆ መሸጥ፣ በመለኪያ መሣሪያዎች ማጭበርበር፣ ምርትን በመደበቅ ሰው ሠራሽ እጥረት መፍጠር፣ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ፣ ጊዜያቸው ያለፈና ጥራታቸው የተጓደለ ምርቶችን መሸጥ እንዲሁም ያለ ንግድ ፈቃድ መሥራት ዋነኞቹ ናቸው።
እነዚህን ሕገወጥ አሠራሮች ለመከላከልና ጤናማ የገበያ ሥርዓትን ለማስፈን የንግዱ ማህበረሰብ ሕጋዊ የንግድ መንገድን በመከተል ለሸማቾች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በሥልጠናው ላይ አጽንኦት ተሰጥቷል።
በሥልጠናው ላይ ከዳርቻ ዝግባቦቶ ከተማና ከአካባቢው ቀበሌዎች የተውጣጡ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
See less









