የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

በጤናማ ፉክክርና በትብብር ላይ የተመሰረተ፣ ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ

በጉራጌ ዞን የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መጪው ምርጫ በጤናማ ፉክክርና በትብብር ላይ የተመሰረተ፣ ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ።

‎

ሚያዝያ 07/2018 (አገና)‎

የዞኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የምርጫ ሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ በሚያስችል የጋራ ሥርዓት ላይ በሰፊው ተወያይተዋል።

‎

‎የውይይት መድረኩን የመሩት የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል፤ መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያና ደንብ መሠረት በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ጠንካራ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

‎

‎እንደ ዞን በሁሉም መዋቅሮች ሰላማዊና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀው ያሉ ጉድለቶችንም በጋራ እያረሙ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።

‎

‎አቶ አለማየሁ አክለውም፣ ፓርቲዎች ከመገፋፋት ይልቅ በመቀራረብና በሐሳብ የበላይነት በመፎካከር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እየተቻለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የምርጫ ሂደቱ የተሳካና ማህበረሰቡን የሚመጥን እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

‎

‎የምክር ቤቱ ፀሐፊና የኢዜማ አባል ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ያበኬር፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ለሀገር ልማትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ዋነኛው መሠረት መሆኑን አንስተዋል።

‎

‎የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ ዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ፓርቲዎች በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

‎

‎የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ አባል አቶ ሄኖክ አብድልሰመድ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ አባላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በየጊዜው በሚደረጉ ምክክሮች ጠንካራ ጎኖችን የማስቀጠልና ክፍተቶችን የመሙላት ስራ የሚከናወን መሆኑን ገልፀዋል።

‎

‎ወቅቱን የዋጀና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ማዳበር አለብን ያሉት አቶ ሄኖክ፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተቀመጡ የጋራ አሰራርና ስርዓት መከተል ለዴሞክራሲ ግንባታው ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

‎

‎በጎጎት ፓርቲ የጉራጌ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ አባል ዶክተር አብዱልአዚዝ ሙሰማ፤ የሐሳብ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ማከናወን የሁሉም ፓርቲዎች ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

‎

‎ተቀባይነት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ሕግን የተከተለ ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

‎

‎ሌሎች የመድረኩ ተሳታፊዎችም በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ሂደቱን ለመከታተልና ደጋፊዎችን ለማስተዋወቅ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በውይይት እየፈቱ መሆናቸውን ጠቅሰው ፣ ወደፊትም ይህንኑ የውይይት ባህል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

‎

‎አሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመፍጠር በመንግስት በኩል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በየደረጃው የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም ረገድ በሁሉም የምርጫ ክልል የጋራ ምክር ቤት ምክክሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል መባሉን ከጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።