





ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን በትምህርት ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮች በማረም የትምህርት ቤቶች ደረጃ እና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አመታዊ የትምህርት ጉባኤ ፕሮግራም በወልቂጤ ከተማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል እንደገለፁት ትውልዱ በማንኛውም የስራ መስክ ተሰማርቶ ውጤታማ ህይወት እንዲኖረው ትምህርት መማር እንደሚጠበቅበት የመከሩ ሲሆን ለዚህም በትምህርት ላይ የሚነገሩ ተገቢ ያልሆኑ አመለካከቶች ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት።
የዞኑ ማህበረሰብ ለትምህርት ሲባል ያለውን ሁሉ የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት አቶ አለማየሁ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እና ለጉራጊኛ ትምህርት ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው አስገንዝበዋል።
አመራሩ የትምህርት ተግባር ፓለቲካዊ ትርጉም በመስጠት ከሌሎች ወቅታዊ ስራዎች ጋር አቀናጅቶ በመስራት የዞኑ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት ዋና ተጠሪው።
በጉባኤው የተገኙት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በንግግራቸው የትምህርት ስራ እጅግ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ስራው በትግስ፣በትጋትና በቅንጅት መስራት ይጠይቃል ብለዋል።
የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ችግሮችን በጥናት መደገፍ፣የተማሪዎች ስነ ምግባር ማሻሻል እና የትምህርት ግብአት ማሞላት ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው በዞኑ የተጀመረው የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን በትምህርት ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮች በማረም የትምህርት ቤቶች ደረጃ እና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ አስከብር ወልዴ ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማረያም የትምህርት ዋና አላማ እውቀት ፣ክህሎትና አመለካከት በማስተካከል እና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎች መፍጠር ነው።
ይሁን እንጂ ባለፉት አመታት ጥራታቸው የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ባለመገንባታቸው፣አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ግብአቶች ባለመሟላታቸው እና ትምህርት ቤቶች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ባለመመራታቸው በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ ሳይመጣ ቀርቷል።
በዞኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን በቀጣይም ይህንን ለማስቀጠል ባለሀብቱ፣የግል እና የመንግስት ተቋሟት ፣አጋዥ ድርጅቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራው ያለ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲሱ ስርአተ ትምህርት የሚያስተምሩ ከ2 ሺ በላይ መምህራኖች ስልጠና ተሰጥቷል ያሉት አቶ መብራቴ የትምህርት ውጤት ለማምጣት የመምህራን ኮሌጅ እንዲኖር እና በዞኑ የተጀመረው የአዳሪ ትምህርት ቤት በአፋጣኝ መማር ማስተማሩ እንዲጀምር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ትውልዱ ምንም እንኳ እውቀትና ክህሎት ኖሮት እንዲሁም በቴኬኖሎጂ ቢራቀቅም ተገቢ ስነ ምግባር ከሌለው እውቀቱ እና ብቃቱ ለሀገርም ሆነ ለቤተሰብ አገልግሎት ስለማይሰጥ በተለይ የእምነት ተቋማት እና ወላጆች ጨምሮ ሁሉም ሰው የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አቶ መብራቴ አሳስበዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አካላት እና የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል መምህራን፣ተማሪዎች እና ወላጆች ጥብቅ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
አክለውም በአመቱ በተፈጠሩ የትምህርት ንቅናቄዎች ለትምህርት ግብአት የሚሆኑ ቁሳቁሶች የተሟሉ ቢሆንም አሁንም በትምህርት ቤቶች እየተስተዋሉ ያሉ የላብራቶሪ፣የመጽሀፍት፣ የወንበር እና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ማሟላት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በዞኑ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የተጀመሩ ስራዎች ያደነቁት ሀሳብ ሰጪዎቹ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ ፣ ስነ ምግባራቸው እንዲስተካከል ፣ ኩረጃን እንዲጸየፉ መምህራን እና ወላጆች ጨምሮ የእምነት ተቋማቶች ሚናቸው ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በእለቱም በ6ኛ ፣በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን በተጨማሪም ለትምህርት ዘርፉ ድጋፍ ላደረጉ የበጎ አድራጊ ማህበራቶች፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ግለሰቦች የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በተያያዘም በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራቶች
1ኛ እኖር ወረዳ ፣2ኛ ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ፣ 3ኛ ቸሀ ወረዳ ሲሆኑ
አንድ መጽሀፍ ለአንድ ተማሪ ንቅናቄ ደግሞ
1ኛ የቸሀ ወረዳ፣
2ኛ እዣ ወረዳ
3ኛ እኖር ወረዳ ናቸው።
በሀገር አቀፍ ፣በክልላዊና በዞናዊ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት ካመጡት መካከል
1ኛ ጌታ ወረዳ
2ኛ እንደጋኝ ወረዳ
3ኛ ምሁር አክሊል ወረዳ በመሆን ያጠናቀቁ ሲሆን ለሁላቸውም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በጉባኤው የመሪያው የ2016 ዓ.ም አጠቃላይ የስራ ሪፖርት እንዲሁም የ2017 ዓ.ም የንቅናቄ እቅዶች ቀርበው ውይይት በማድረግና ከመዋቅሮች ጋር የግብ ስምምነት በመፈራረም መድረኩ ተጠናቋል ።






