






በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በከፍተኛ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው
መጋቢት 12/2018 ዓ.ም
በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በከፍተኛ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው።
ማህበረሰቡ “ድምፄን በካርዴ እመርጣለሁ፤ ተወካዮቼን በምርጫዬ” በሚል መርሀ ግብር የዴሞክራሲ መብቱን ለመጠቀም በንቃት እየተመዘገበ ይገኛል።
በየቀበሌው የተዘጋጁ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች ላይ ወጣቶችና ማህበረሰቡ በመሳተፍ ወደ ምዝገባ ጣቢያዎች በመምጣት የመራጭነት ካርዳቸውን ለመውሰድ እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ለዘላቂ ሰላም አንዱ የመፍትሄ አማራጭ በመሆኑ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ይታወቃል።
በምዝገባው ቦታ ያገኘናቸው አንዳንድ ነዋሪዎች እንዳሉት ድምፃቸው በሀገራዊ ምርጫ ውስጥ እንዲሰማ በመራጭነት መመዝገብ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ ሌሎች ዜጎችም ይህን ዴሞክራሲያዊ ግዴታ እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ አሻራቸውን በማሳረፍ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዜጎች አገር ወዳድነታቸውን በተግባር ከሚያሳዩባቸው መንገዶች አንዱ በምርጫ ንቁ ተሳታፊ በመሆን እንደሆነ በማንሳት ለዚህ ደግሞ ቅድሚያ የመራጭነት ካርድ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።
የምርጫ አስፈጻሚ ባለሙያዎችም የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ በተደነገጉ የምርጫ ህጎችና መመሪያዎች መሰረት በሰላማዊ እና በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑንም ገልፀዋል።
አክለውም የምርጫ ጣቢያዎች ዝግጁ ሆነው እያስተናገዱ መሆናቸውና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
ድምፅ መስጠት መብት ብቻ አይደለም የዜግነት ኃላፊነት እንጅ!







