






“አንትሮሸት” እናቶች የእናትነት ወጋቸው ጎልቶ የሚወጣበት የሚከበሩበት የሚያርፉበት እና ተስፋን የሚሰንቁበት በመሆኑ በተጠናከረ መንገድ ማክበር እንደሚገባ ተገለፀ።
ጥር 14/2018 ዓም
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የ2018 ዓ/ም የአንትሮሸት ( የእናቶች ቀን) በዓል በድምቀት ተከበረ።
የእዣ ወረዳ ም/የመንግስት ተጠሪ አቶ አብዱራህማን ሀሰን ለዘመናት ሴቶች ከወንዶቹ እኩል ነጻነት ሳይሰጣቸው የኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲሁ የፖለቲካ ተሳትፏቸው ሲነፈጉ እንደነበር ጠቅሰው ።
በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ግን የአሜሪካ ሴቶች ጥያቄም ሆነ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ድንጋጌ በፊት ስለሴቶች ነጻነት በማይታመን መልኩ በቃቄ ውርድወት ፊት መሪነት ውጤት በማምጣት የሴቶች መብት የተከበረበት መሆኑን ገልጸው።
አሁንም እናቶች የእናትነት ወጋቸው ጎልቶ የሚወጣበት የሚከበሩበት የሚያርፉበት እና ተስፋን የሚሰንቁበት ያማረ እና የደመቀ እናቶች ደስታቸውን የሚገልጹበት እና ትውልድን የሚመረቁበት በአል ስለሆነ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ይህን በዓል ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሻገር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእዣ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ አሰለፈች ክብሩ ዲሞክራሲና ስልጣኔ ቀድሞ የጀመሩ የአውሮፓ ሀገራት ስለሴቶች መብት ክብርና ነፃነት በተገቢው በህገመንግስታቸው ሳይጀመሩ የጉራጌ ማህበረሰብ ለሴቶች ለእናቶችና ልጃገረዶች መብትና ነፃነት ለማጎናፀፍ የሚያስችል ሀሳብ አፍልቆ በተግባር ለማሳየት የቻለ መሆኑን ገልጸው ።
ይህንንም ተከትሎ በወረሃ ጥር እናቶች የሚከበሩበት የሚደሰቱበት የሚያርፉበት ተስፋ የሚሰንቁበት ወር እንደሆነ ተወስኖ የአንትሮሸት (የእናቶች በዓል) ሲከበር መቆየቱን ገልፀው ።
እንደ ወረዳ ለሶስተኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው ይህ በዓል ነገር ግን ከ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ዞኑ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአሉ በሁሉም ወረዳዎች እየተከበረ እንደሚገኝ ጠቅሰው።
ከዚሁ በዓል ጋር ተያይዞ በወረዳ ደረጃ ለሦስተኛ ዙር ሞዴሊንግ ስራ በበርካታ ተግባራቶች ሲሰሩ መቆየቱን ገልጸው በሶስተኛ ዙር ሞዴሊንግ ከተሰራባቸው ቀበሌዎች አንዱ ገደብ ቀበሌ እንደሆነ አመላክተው ለሁለቱም በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እናቶችም በበዓሉ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽና በመመረቅ እንዲሁም በሞዲሊግ ስራ ላይ ከፊት ለነበሩ እናቶች እና ለቀበሌው አመራር የእውቅና ሰርተፍኬት በመስጠት በአሉ ተከብሮ ውሏል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።








