







የአርሶ አደሩን አኗኗር የሚያዘምን የገጠር ማዕከላት ቤት ልማት ኢኒሼቲቭ ይፋ ተደረገ
መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አገና)
በእዣ ወረዳ የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን መሰረተ ልማት በማሟላትና የተሻሻሉ ቤቶችን በመገንባት የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለማዘመን ያለመ የምክክር መድረክ ከወረዳው አመራሮች ጋር ተካሂዷል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ በገጠር የሚገኘውን ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የገጠር ማዕከላት ቤት ልማት ኢኒሼቲቭን በቅንጅት መተግበር ያስፈልጋል። የገጠር አካባቢዎች በፍጥነት ወደ ከተማነት እያደጉ በመሆኑ፣ ይህንን እድገት በፕላንና በዲዛይን መምራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጉራጌ ብሔር መገለጫ የሆነውን “ጀፎረን” ተከትሎ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችና አጥሮችን በመገንባት በሁሉም መዋቅሮች ሞዴል መንደሮችን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው የሚገነቡት ቤቶች ለሰው መኖሪያ፣ ለቤት እንስሳት መጠለያ እና ለምግብ ማብሰያ (ኩሽና) የተለዩ ክፍሎች እንዲኖሯቸው ተደርገው በወጥ ፕላን የሚገነቡ ይሆናል። በተጨማሪም ከሌማት ትሩፋት ጋር በማተሳሰር በአካባቢያቸው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲለማባቸው ይደረጋል ብለዋል።
ከመሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂ አኳያም የቤት ልማቱ ከመንገድና ከንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጋር ተሳስሮ የሚከናወን ሲሆን፣ አካባቢን የሚጠብቁና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
የእዣ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አየለ በበኩላቸው፣ ከ78 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በገጠር እንደሚኖር ጠቁመው፤ የመሬት አጠቃቀም ስርዓቱን በማዘመን ውብና ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በወረዳው ውስጥ የህዝብ ቁጥራቸው ከ500 እስከ 2,000 የሚደርስባቸው “ከተማ ቀመስ” የገጠር ማዕከላት የኢኒሼቲቩ ቀዳሚ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልፀዋል።
ይህ አዲስ አሰራር ከገጠር ወደ ትላልቅ ከተሞች የሚደረገውን ፍልሰት በመቀነስ፣ አርሶ አደሩ ባካባቢው ተረጋግቶ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው በውይይቱ ላይ ተመልክቷል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።







