






‹ያጋ ቃዋ››- የጉራጌ ማህበረሰብ የቡና ሥነ-ሥርዓት
============================
የጉራጌ ማህበረሰብ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ከሚያቀራርብላቸው ወይም ከሚያጠነክርላቸው መልካም እሴቶች መካከል ‹‹ያጋ ቃዋ›› የሚሉት የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት አንዱ ነው፡፡
የጉራጌ ማኅበረሰብ ካለበት ቀዬ አቅራቢያ ከሚገኙ ጎረቤቶቹ ከሦስት እስከ ስድስት አባላት በመሆን ቃዋ (ቡና) ይጠጣሉ፡፡
የቡና አፈላል ሒደቱ የሚከናወነው ተራ በተራ ነው፡፡ ዛሬ በአንዱ አባ ወራ ቤት ከተፈላ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተራውን ጠብቆ በሌላኛው አባወራ ቤት ይፈላል፡፡
ይህ ዓይነቱ የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት “ያጋ ቃዋ” በመባል ይታወቃል፡፡ ጠዋት ላይ የሚካሄደው የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት ያጋ ቃዋ ሲባል መሸት ሲል ተጠራርተው የሚጠጡት ቡና ደግም ዊጔር ቃዋ (ሸንጎ ቡና) ተብሎ ይጠራል፡፡
ያጋ ቃዋ እጅግ በጣም ተወዳጅ የሆነ የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት ነው። ሰዎችን እርስ በርስ የሚያገናኝና የሚያዋድድ፣ የሚያፋቅርና የሚያስተሳስብ ስለሆነ ጉራጌዎች ለያጋ ቃዋ ልዩ ትኩረት ይሰጡታል፡፡
ባለተረኛዋ እማወራ ሌሊት ወፎች ከመንጫጫታቸው በፊት አስቀድማ በመነሳት ‹‹ቦሄ ያትየደርሄ ጔታ ቦሄ አወሬ›› (ሰላም ያሳደርከኝ አምላክ ሰላም አውለኝ) በማለት ለአምላኳ ምሥጋና ካቀረበች በኋላ ተጣጥባ ቡና የማፍላት ዝግጅቷን ትጀምራለች፡፡
የቡና አቆላሉ ሥነ ሥርዓቱ ሌላ ትዕይንት ይፈጥራል፡፡ ቡናው ይታጠባል፣ ይቆላል፣ ይወቀጣል፡፡ ከቀርከሃ የሚዘጋጀው ባህላዊ የቡና መቁያ ማንቁሬት ተብሎ ይጠራል፡፡
ባህላዊ የቡና መቁያ ምጣድ፣ ምዳድ ሲባል ባህላዊ የቡና መውቀጫ ደግሞ ዳንጋሳ (ሙቀጫ) ተብሎ ይጠራል፡፡ በሸክላ የተሠራ ባህላዊ ቡና የሚፈላበት መሣሪያ ጀበን (ጀበና) በመባል ይታወቃል፡፡ ጀበናው እሳት ላይ የሚጣድበት በሸክላ የተሠራ ደግሞ ጎንዝየ (ጉልቻ) ተብሎ ይጠራል፡፡ ቡናው ሲቆላ ምጣዱ ላይ ይወዛል፡፡
የቡናው መዓዛ አካባቢውን ሲያውደው ሰውነት ላይ አንዳች ስሜት በመፍጠር አፍ አውጥቶ ከሩቅ ኑ ቡና ጠጡ ብሎ ይጣራል፡፡
ጉራጌዎች ቡና በሚጠጡበት ሰዓት ቤት ያፈራውን የቡና ቁርስ ያቀርባሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ቆሎ፣ አተርና ባቄላ የመሳሰሉ ጥራጥሬዎች በብዛት ይዘወተራል፡፡ እንደ ወቅቱ ሁኔታ ድንችም ቡና ቁርስ ላይ ይቀርባል፡፡
ጉራጌዎች ፆም ወይም የፆም ወቅት ካልሆነ በስተቀር ቡና በቅቤ ነው የሚጠጡት፡፡ የቅቤ ቡና መጠጣት የሰውነት እርካታ ከመስጠቱም በላይ ፍቱን መድኃኒት ነው ብለው ያስባሉ፡፡
ብዙ ጊዜ ቡና ውስጥ ተደርጎ የሚጠጣ ቡና በቅመማ ቅመም የተዘጋጀ ያልተነጠረ (ጥሬ) ቅቤ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቅቤ ኡፋ ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ጉራጌዎች ባህላዊ የሆነ የቅቤ አዘገጃጀት ዘዴ አላቸው፡፡ በቅመማ ቅመም ታሽቶ የተዘጋጀ ቅቤ ከምግብ ጋር ተሠርቶ ሲበላ እጅግ ከመጣፈጡ የተነሳ ጣት ያስቆረጥማል፡፡
ጉራጌዎች የሚያፈሉት ቡና ይጣፍጣል፡፡ የቅቤ ቡናቸው እጅግ ተመራጭ ነው፡፡ አባወራው ቡና ወደ ተጠራበት ቤት ከመሄዱ በፊት ፈረስ፣ አህያ ወይም የሚያርስበት በሬ ካለው አስቀድሞ ወደ መስክ ያሰማራል፡፡
እማወራዋም የወተት ላም እቤቷ ካለች ወተቷን ካለበች በኋላ ነው ወደ ተረኛዋ ቡና አፍዩ ቤት የምታመራው፡፡ በጉራጌዎች የምትታለብ ላም ‹ኤብ ራም› ይባላል፡፡
ኤብ ማለት ወተት ማለት ሲሆን ራም ደግሞ ላም ነው፡፡ ያጋ ቃዋ ጠጪ አባላት በተረኛ ቤት ይሰባሰባሉ፤ አምሽቶ ያነጋን አምላክ ይመስገን ቀኑም በሰላም ያውለን እያሉ የከበረ ሰላምታቸውን ይለዋወጣሉ፡፡ ጎረቤታሞቹ ሲገናኙ ጨዋታው ይደራል፡፡
ሽማግሌዎች ጨዋታቸውን ያደሩታል፡፡ ቡናቸውን እየጠጡ ያወጋሉ፡፡































