የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

======ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀት ማጠናከር እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ፅ/ቤት አስታወቀ ።

ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀት ማጠናከር እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ፅ/ቤት አስታወቀ ።

ፅ/ቤቱ የሴቶች ልማት ህብረት ለማጠናከር እና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ከወረዳው ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት እና ከወረዳው ሴቶች ሊግ ፅ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

የእዣ ወረዳ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ አብድራህማን ሀሰን በንቅናቄ መድረኩ ወቅት እንደገለፁት ሴቶች በልማት ህብረት አማካኝነት በሚከናውኑት ተግባራት በማህበራዊ ፡ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኩ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየተለወጠ ይገኛል።

ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ፡ በሌማት ትሩፋት በገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበራት በማጠናከር ፡ ጾታዊ ትንኮሳን መከላከል ላይ ዋንኛው ተዋናይ መሆን አለባቸው ያሉት ሀላፊው ከዚህ በተጨማሪ የትምህርት ተሳትፎን ፡ የጤና ፓኬጅን ተግባራዊ በማድረግ ፡ የማህፀን ጫፍ ካንሰር እና ወባን መከላከል ላይ በትኩረት መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።

የእዣ ወወዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ በሀገሪቱ ብሎም በወረዳው የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በሴቶች ላይ የሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመከላከል የክትባት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የተለያዩ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁን ትኩረት የሚያስፈልገው ነው ብለዋል።

ሌላው በወረዳው እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የወባ በሽታ ለመከላከል በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም የወረርሽኑ መጠን ከቁጥጥር በላይ ነው ያሉት አቶ መሀመድ ማህበረሰቡ ወባን መከላከል የሚያስችሉትን የአጎበር አጠቃቀም ፡ የውሃ ማፋሰስና ሌሎችም መከላከላከያ ዘደዎች ከመጠቀም ጋር ያለው መዘናጋት ቶሎ ማረም እንዳለበትም ጨምረው ገልፀዋል።

የእዣ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ አሰለፈች ክብሩ እንደ ወረዳው 424 የልማት ህብረቶች የተደራጁ ሲሆን 1492 የ1ለ10 ጥምረቶች እንዲሁም 12840 የሴቶች ልማት ህብረት አባላት መደራጀታቸውንም አስረድተዋል ።

ሴቶች ቁጠባን ባህል በማድረግ በሚያከናውኑ የልማት ስራዎች ከሚያገኙት ቁጠባ በግልም ይሁን በህብረት ቁጠባ በመቆጠብ በተለያዩ ገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ ማሳደግ አለባቸው ያሉት ወ/ሮ መሰለች በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ ሴቶች የገቢ አማራጮችን በማሳደግ የሌማትን ቱሩፋት ጨምሮ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት ይገባልም ብለዋል።

ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት በመንግስት ደረጃ በግንዛቤና በተለያየ ደረጃ በተደረገላቸው ድጋፍ ቁጠባ በመቆጠብ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይም የሴቶች የልማት ቡድን ሥራን ለአንድ ሴክተር የሚተው ባለመሆኑ በተጠናከረ መንገድ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም የድርሻዎን መወጣት እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረው ተናግረዋል ።

በእለቱም ከወቅታዊ ጤና አጠባበቅ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሰነዶች በአቶ መሀመድ ሰይድ ለተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን በሴቶች አደረጃጀትና ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረጉ የተለያዩ ሰነዶች በእዣ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ አሰለፈች ክብሩ እና በእዣ ወረዳ ሴቶች ሊግ ፅ/ቤት ሀላፊ በወ/ሮ ወይንሸት ፈቀደ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።