








ሸማቹ ህብረተሰብ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች በጤና ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት በመረዳት ግዢ በሚፈፅምበት ወቅት የምርቶቹ መጠቀሚያ ጊዜና የጥራት ደረጃ ማረጋገጥ እንዳለበት ተገለፀ ።
ህዳር 26/2017 ዓም
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ፅ/ቤት ጊዜ ያለፈባቸው የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችና የታሸጉ የሀይላንድ ለስላሳ መጠጦች በማሰባሰብ የወረዳው የህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ ሀይል አባላት በተገኙበት የማስወገድ ስራ ሰርቷል ፡፡
በእለቱም የእዣ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ በለጠ ሳህሌ እንደገለፁት ሸማቹ ህብረተሰብ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች በጤና ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት በመረዳት ግዢ በሚፈፅምበት ወቅት የምርቶቹ መጠቀሚያ ጊዜና የጥራት ደረጃ ማረጋገጥ አለበት።
ፅ/ቤቱ የሸማቾችን መብት ከመጠበቅ አንፃር ከተለያዩ ነጋዴዎች ጋር በተለያየ ወቅት የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በመስራት ከነጋዴዎቹ ጋር የጋራ መግባባት እየተፈጠረ መሆኑን ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
ለንግዱ ማህበረሰብ ቀልጣፋና ፍትሀዊ የንግድ ስርአት ለመፍጠር አቅዶ በትኩረት በመስራት ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ በለጠ በተሰራው የቁጥጥር ስራም ጥሩ መሻሻሎች መኖራቸውንና ከድርጊታቸው ማይቆጠቡ ካሉ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም ተናግረዋል።
በፅ/ቤቱ የኢንስፔክሽንና ሪጉሌሽን ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሽለጋ ምራኒ በበኩላቸው የተወገዱ ጊዜ ያለፈባቸው የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶችና የታሸጉ የሀይላንድ ለስላሳ መጠጦች ፡ የፀጉር ቅባቶች ፡ የህፃናት ምግቦችና ሌሎችም ሲሆኑ በቁጥር 698 መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ሸማቹ ማህበረሰብ እንዲዚህ አይነት ችግሮች ሲገጥሙት ወዲያውኑ ለፅ/ቤቱ በማሳወቅ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በጋራ መከላከል እንደሚገባም አቶ ሽለጋ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምርቶቹ የተወገዱት ግብረ-ሀይል በመወያየት ሲሆን በቀጣይም የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች በማጠናከር በህብረተሰቡ ላይ የጤና ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ ምርቶች የማስወገዱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።







