





=====የማህበረሰቡን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ይበልጥ በመጠቀም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው ወገኖች ለመደገፍ በሚደረው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተገለፀ።
የእዣ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ፅ/ቤት በወረዳው የሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ በማስተባበር ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች የገና በዓልን አስመልክቶ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በድጋፍ ወቅት እንዳሉት መሰል ድጋፎች በዘዘላቂነት ከችግር የሚያወጡ አለመሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ ተጋላጮች ራሳቸው የሚችሉበት መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
እንደ ወረዳ ይህ ተግባር በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ዘውዱ በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ ድጋፍ የሚሹ ወገኖቻችን ችግሮቻቸው በማቃለል ወጣቱ ብሎም መላው ማህበረሰቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእዣ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ይድነቃቸው ሙሉጌታ በበኩላቸው በዚህ ተጠቃሚ የሆኑት እናትና አባታቸው ያጡ ህፃናት፣ የዘማች ቤተሰብና ተጋላጭ አረጋዊያን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑ ገልፀዋል።
አክለውም ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ከንግዱ ማህበረሰብ የተሰበሰበው ሲሆን አጠቃላይ ድጋፉ ከ64ሺ ብር በላይ ወጪ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸውም ወገኖች በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ለወረዳው መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የወረዳው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብይ ኮሚቴ አባላትና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።







