
OK በረኪና የተሰኜዉ ምርት አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ መስፈርትን የማያሟላና የጥራት ችግር ያለበት መሆኑ ስለተረጋገጠ ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር OK በረኪና ላይ በተደረገው የእይታ ፍትሻ መሰረት በምርቱ ላይ የአምራች ስም፣አድራሻና ብሄራዊ የደረጃ ምልክት የሌለው መሆኑንና በተደረገው የላቦራቶሪ የጥራት ፍተሸ ውጤት መሰረት ደግሞ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ መስፈርትን የማያሟላና የጥራት ችግር ያለበት መሆኑን ስላረጋገጠ ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸውን የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች የደረጃ መስፈርት ማሟላታቸውን እንደሚቆጣጠርና ከተዘጋጀላቸው ደረጃ በታች ሆነው በተገኙት ላይም አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የህብረተሰቡን ጤንነት፣ ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የደረጃም ሆነ የየጥራት ቁጥጥርና ክትትል ስራዎችን ያከናውናል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በገበያ ላይ ባደረገው የኢንስፔክሽን ስራ የምርት ስሙ OK በረኪና በሆነው ምርት ላይ ወካይ ናሙና በመውሰድ በተደረገው የእይታ ፍተሸ በምርቱ ላይ ስምና አደራሻ እንዲሁም የደረጃ ምልክት የሌለውና በተደረገው የላቦራቶሪ የጥራት ፍተሸ ውጤት መሰረት በStability እና Sodium hydroxide conent አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ CES 234:2023 የደነገገውን የጥራት መስፈርት ያላሟላ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት እንዲሁም ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ይህን ምንጩ የማይታወቅና የጥራት ችግር ያለበትን ምርት ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም በየደረጃው ባሉ የክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በኩል ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግና ማንኛም ነጋዴ በገበያ ቦታ፣ በንግድ ሱቆች እና ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ይህን ምርት ሲሸጥ ከተገኘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡






