የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

ከቴክኖሎጂና ከፈጠራ ውጪ ብልፅግናን እውን ማድረግ አይቻልም

ከቴክኖሎጂና ከፈጠራ ውጪ ብልፅግናን እውን ማድረግ አይቻልም፦ክቡር አቶ ላጫ ጋሩማ

ሰኔ 2/2018 ዓ.ም (ወልቂጤ)፦የጉራጌ ዞን የ5ኛው ዙር የሳይንስ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራ ዉድድር አውደ-ርዕይ እና የፓናል ውይይት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

“ሳይንስ ይመራናል ቴክኖሎጂ ያስቀድመናል” በሚል መሪ ቃል በጉራጌ ዞን የተካሄደው የ5ኛው ዙር የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር በርካታ የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት ነው።

በፈጠራ ስራዎች ውድድርና ኤግዚቢሽን ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት በአንድ ሀገር ብልጽግናና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲኖር የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች ወሳኝ ናቸው ።

ትምህርት ቤቶች በሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ላይ በትኩረት መሰራት አለባቸው ብለው በፈጠራ ስራዎች የሚሳተፉ ተማሪዎች ፣ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ሌሎች በግል ፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ማበረታታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ በስራ ፈጠራ የሚታወቅ እንደሆነም የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው የህዝባችን ባህልና እሴት የሆነውን የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች አጠናክሮ ማጎልበት እና በዘርፉ የተሻለ ስራ በመስራት የማህበረሰቡ ችግር በዘላቂነት መቅረፍ ይገባል ብለዋል።

ለሳይንስና ለሂሳብ ትምህርቶች የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አንዳለበት ያመላከቱት አቶ ላጫ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች የሚሰሩ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች እንዲሸጋገሩ ለማስቻል የአቅም ግንባታ ስራ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ብለዋል።

በ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ዞናችን የራሱ የሆነ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል፣ባለፉት አመታትም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዞን ትልቅ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ስራዎችን በቴክኖሎጂ የታገዙ፣ ከንክኪ ነፃና፣ጥራት ያላቸው ሆነው በፍጥነት እንዲከወኑ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም እንደገለጹት ለአንድ ማህበረሰብ እድገትና ብልፅግና ዋነኛው መሳሪያ ትምህርት መሆኑን በመገንዘብ፣ የሳይንስ፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ስራዎችን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካትና አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በዞኑ ዘንድሮ ለ5ኛ ዙር የተዘጋጀው የፈጠራ ስራዎች ውድድርና ኤግዚቢሽን ዞኑ ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለእነዚህ ውድድሮችና ለዘርፉ ድጋፍ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ስራ ላይ መዋሉን ሀላፊው ገልጸዋል።

ይህ ዞን አቀፍ ሲምፖዚየም ዞኑን በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወክሉ የፈጠራ ስራዎችን ለመለየትና እውቅና ለመስጠት ያለመ ሲሆን፤ ዘርፉ ካለበት አቅምና ጉድለት አንጻር ገና በጅምር ላይ በመሆኑ በቀጣይ በበጀትና በእቅድ ለመደገፍ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል።

በ5ኛ ዙር የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ውድድድርና ኤግዚብሽን የተገኙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግና ማህበረሰባዊ እሴቶችን ለመገንባትና ለማጉላት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቀጣይነታቸው ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ እንዳሉት ውድድሩ በዋናነት ተማሪዎች የሳይንስና የሂሳብ ትምህርቶች ላይ ዝንባሌ እንዲኖራቸው ፣ችግር ፈቺ ሀሳብና ቴክኖሎጂ መፍጠር እንዲችሉ እንዲሁም ውጤታማና የማህበረሰቡ ቁልፍ ችግር የሆኑ ነገሮችን አዳዲስ ፈጠራና ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በጥራት ማከናወን እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል።

የፈጠራ ስራ ውድድርና አውድ ርዕይ ሳይንስ ይመራናል ቴክኖሎጂ ያስቀድመናል በሚል መሪ ቃል መካሄዱ የዘመናችን እውነታ በግልጽ ያሳየ እንደሆነም ተናግረዋል።

እንደ ሀገር እንደ ክልልና እንደ ዞን ሳይንስን እንደ መመሪያችን ፣ቴክኖሎጂ እንደ መንገዳችን ካልያዝነው ወደ ኋላ እንቀራለን ብለው በዛሬው እለት በውድድሩ የቀረቡ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች የረጅም ጊዜ ጥረት ፣ ተደጋጋሚ ሙከራ የተደረገባቸው ችግር የሚፈቱ ፣ ህይወት የሚያሻሽሉ የሀገሪቱን ልማት የሚያፋጥኑ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች እንደሆኑም አስረድተዋል።

5ኛ ዙር የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች ውድድድርና ኤግዚብሽን ተወዳዳሪዎች ችሎታቸውን ያሳዩበት ፣ በራሳቸው የመተማመንና ወደ ተሻለ መንገድ የሚሸጋገሩበት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ እንደሆነም አስረድተዋል።

በመድረኩ የተገኙት ተሳታፊዎች በበኩላቸው የዞኑ አስተዳደር ለሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ የሰጠውን ትኩረት አድንቀው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አመላክተዋል።