መስከረም /2019 ዓ.ም (አገና)
በእዣ ወረዳ በሁሉም አካባቢዎች መጪው የመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር የወረዳው ፀጥታ ተቋማት ዉይይት በማድረግ በድጋሚ ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።
የእዣ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ከበደ እንደገለፁት መስቀል የጉራጌ ማህበረሰብ በተለየ ድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱና ዋነኛው ሲሆን እንደወረዳችንም በዓሉን ለማክበር የአካባቢው ተወላጆችና የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ህዝቦች ወደ ወረዳችን ይመጣሉ ብለዋል።
በመሆኑም በዓሉ ሐይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱ ሳይለቅ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የፀጥታ አባላት አስቀድሞ መሰማራታቸው ገልፀዋል።
ሀላፊው አክለውም በቀጣይም ማህበረሰቡ ከፀጥታ አካላት በመቀናጀት ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ያመላከቱ ሲሆን በተለይም በትራፊክና ፍሰት አደጋ እንዳይከሰት ፍጥነትን መቀነስ፣ መንገድ ላይ እንስሳት አለመንዳትና ግራ ጠርዝ ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት ገልፀዋል።
የወንጀል መከላከል ስራን በማጠናከር በተለይም ስርቆት፣ በገበያ ሀሰተኛ የብር ኖት/ማጭበርበር/ መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ የገለፁት ሀላፊው የሴቶች እና ህፃናት ጥቃት እንዳይከሰት፤ የግጭት መከላከል ስራና የእሳት አደጋ እንዳይኖር በግል ቤትና በደመራ ቦታ የኤክትሪክ መስመር አካባቢ የጥንቃቄ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
የተለየ ነገር ሲከሰት በቀበሌ ከሚገኙት የሚሊሻ አባላት፣ ከፖሊስ እና ከፀጥታ ተቋም መረጃ በመለዋወጥ የመከላከልና ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራም አመላክተዋል።
የእዣ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ም/ኢንፔክተር ዳኛቸው አትርፎ በበኩላቸው የፀጥታ አባላት በዓሉ በሰላም እንዲከበር ለማድረግ ከቀበሌ የሚሊሻ አባላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ገልፀው ወንጀል እንዳይከሰት በመስራት ከተከሰተም ህግ የማስከበር ስራ በተገቢው እንደሚሰራ አመላክተዋል።
አዛዡ አክለውም በየቀጠናው አባላት ለዚሁ ስራ መመደባቸውና ማህበረሰቡ ማንኛውም አጠራጣሪ ተግባር ሲመለከት ከፀጥታ አካላት እንዲተባበር አሳስበዋል።











