የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

የቆጠር ገድራን የተፈጥሮ ደን

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ የሚገኘው የቆጠር ገድራ የማህበረሰብ የተፈጥሮ ደን ዘለቄታዊ የደን አያያዝ እቅድ ሰነድ ማጽደቂያ መድረክ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

==============================================================================

መስከረም 11/2019 ዓ.ም (አገና)

የቆጠር ገድራን የተፈጥሮ ደን ከጥፋት ከመታደግ ባለፈ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሳይንሳዊ መንገድ ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።

የጉራጌ ማህበረሰብ ጉርዳ ባህላዊ የተፈጥሮ ደን ልማት አስተዳደር ከ135 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን ጠብቆ ማቆየት መቻሉን ተገልጿል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብራሃም መጫ እንዳሉት ኢትዮጵያ ካሏት ጸጋዎች አንዱ የተፈጥሮ ሀብቷ ስነ ምህዷሯና የደን ሀብቷ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጉራጌ አካባቢ ተፈጥሮና ባህልን በመያዝ፣ በመጠበቁ እንዲሁም በመንከባከብ ለኢትዮጵያ ሞዲል የሚሆን አካባቢ እንደሆነም አመላክተው የቆጠር ገድራ ደን ለማልማት እየተደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ደን ልማት የምርምር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዳመነ ዳሮታ እንደገለጹት፤ የቆጠር ገድራ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ደን በአካባቢው ባህላዊ የደን አስተዳደር ስርዓት አማካኝነት ለዘመናት ተጠብቆ የቆየ ድንቅ ተፈጥሯዊ ሀብት ነው።

ደኑ በቆጠር ገድራ፣ ሻመነ፣ ዋሳመር እና በአካባቢው በሚኖሩ የቤተሰቡ ተወላጆችና የማህበረሰብ አባላት በተመሰረተው የቆጠር ቤተሰብ ልማት ማህበር ባለቤትነት ሲጠበቅ መቆየቱን አቶ ዳመነ ገልጸዋል።

ማህበሩ እንደ እድር ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን፣ ባህላዊና መንፈሳዊ እምነቶችን፣ ወጎችንና ድንጋጌዎችን በመጠቀም ደኑ እንዳይደፈርና ተፈጥሯዊ ይዘቱ እንዳይበላሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አብራርተዋል።

ይህ ባህላዊ የደን አጠባበቅ ዘዴ ውጤታማ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በምሳሌነት የሚጠቀስ የደን አስተዳደር ልምድ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ የደኑን ህልውናና ዘላቂነት የበለጠ ለማረጋገጥ ባህላዊ እውቀቱን ከሳይንሳዊ አሰራር ጋር ማጣመር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።

በዚሁ መሰረት በኢትዮጵያ ደን ልማት እና በቆጠር ቤተሰብ ልማት ማህበር መካከል በተደረገው ትብብር፣ የተመራማሪዎችንና የማህበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ ያረጋገጠ ጥልቅ የደን ዳሰሳ ተካሂዶ ዘላቂ የደን አስተዳደር እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ እንዳለ ስጦታው እንዳሉት የቆጠር ገድራ የተፈጥሮ ደን በማልማት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የጉራጌ ማህበረሰብ ጉርዳ ባህላዊ የተፈጥሮ ደን ልማት አስተዳደር ከ135 ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን በዘላቂነት ለማልማትና ጠብቆ ለማቆየት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በእዣ ወረዳ የሚገኘው የቆጠር ገድራ የማህበረሰብ ተፈጥሮ ደን ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማልማት እንዲቻል ማህበረሰቡ በተገቢው ጥበቃ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአየር ሁኔታ ተጽኖ በማህበረሰቡ ላይ እንዳይደርስና የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ደን ልማት ባለሙያተኞች በቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን ላደረጉት ጥናትና ምርምር በዞኑ አስተዳደር ስም ከልብ አመስግነዋል።

በመድረኩ የተገኙት የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ እንዳሉት የቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን ከ135 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረና ሲሆን ደኑን የበለጠ ለማልማትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተደረገው ሳይንሳዊና ባህላዊ የምርምር ጥናት ወሳኝ እንደሆነም አመላክተዋል።

ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እድገታቸው ያቆሙ ዛፎችን የማሳሳት ስራ በመስራትና በምትካቸው ሌላ ዛፍፎ በመትከልና በደኑም የአካባቢው ወጣቶችና ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል መፈጠር እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘገባው የጉራጌው ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ነው።