






እንደ እዣ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራቶች የአርሶአደሩ ህይወት ከመቀየርም አልፎ ለክልሉ የምርጥ ዘር ግብዓት ጭምር ተመራጭ እየሆነ እንደሚገኝ ተገለፀ።
ህዳር 3/2019 ዓ.ም (አገና)
በእዣ ወረዳ የግብርና ልማት ሥራዎች የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል::
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በሚከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎችን በተግባር ለመመልከት፣ የአርሶ አደሩን የልማት ተሳትፎ ለመከታተልና በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለመለየት የተዘጋጀው የመስክ ጉብኝት በወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት ተካሄዷል።
የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ በግብርና ዘርፍ የተለያዩ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም ከውጭ በሚገባ ማዳበሪያ ላይ ጥገኝነትን በመቀነስ በአካባቢው በተፈጥሮ የሚዘጋጅ ማዳበሪያን/ቨርሚ ኮምፖስት/ የማምረትና የመጠቀም ሥራ ሊስፋፋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ እዣ ወረዳ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራቶች የአርሶአደሩ ህይወት ከመቀየርም አልፎ ለክሉሉ የምርጥ ዘር ግብዓት ጭምር ተመራጭ እየሆነ መሆኑንም ገልፀዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀም ለማዳበሪያ የሚወጣውን ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ለአፈር ጤንነትና ለምርቱ ጥራት ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ተግባሩን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር በግብርና ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስቀጠል የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከርና በአፈርና ውሃ ጥበቃ የተሰሩ ሥራዎችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
የእዣ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መቻል ተሰማ በበኩላቸው፣ በበርካታ ቀበሌዎች በተለያዩ የሰብልና የእንስሳት ምርቶች የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሥራ በተሻለ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንንም ተሞክሮ በሁሉም ቀበሌዎች ማስፋፋትና አርሶ አደሩን ከራሱ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የሚያቀርብ አምራች ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የግብርና ለውጥ በሁሉም የማህበረሰብ ክፍልና በየቤተሰቡ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ኃላፊው፣ ተግባሩን ውጤታማ ለማድረግ የባለሙያዎችን፣ የአመራሩንና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማቀናጀት መምራት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በተለይም በገበያ ፍላጎትና በባለሙያ ምክረ ሐሳብ መሠረት ምርትን ማቀድ፣ ባለሙያዎችም በሞዴልነት በመቅረብ ማህበረሰቡን ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከሰብዓዊ ድጋፍና ከተረጂነት በራስ አቅም ወደ ሚቆም ማህበረሰብ ለመሸጋገር በወረዳው በመንግስት አቅም የተለያዩ የምርት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አቶ መቻል ገልጸዋል።
በዚህም በሸህረሞ ቀበሌ 10 ሄክታር መሬት ላይ የጤፍ ኩታገጠም ልማት እየተከናወነ ሲሆን፣በሳቦላና ሻመነ ቀበሌዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተሰራባቸው ማሳዎች በተቀናጀ መልኩ የገብስ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ እተሰራ ሲሆን በተጨማሪም በሻመነ ቀበሌ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን በማጠናከር 1150 የተሻሻሉ የዶዮ ገና በግ ዝርያዎች እና 9,081 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
በመስክ ጉብኝቱ የተሳተፉ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች ላይ ያላቸውን ምልከታና ሀሳብ በማንሳት፣ የታዩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ወደ ሌሎች ቀበሌዎች ማስፋፋትና የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም የግብርና ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ጉብኝቱ በወረዳው የግብርና ልማት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ በተግባር ከመመልከት ባለፈ፣ ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት፣ ክፍተቶችን ለመለየትና ለቀጣይ ሥራዎች የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው።
See less







