
========================================
ጥቅምት 3 /2016ዓ.ም
“ጋበር” የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መጽሀፍቶችና የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለእዣ ወረዳና ለአገና ከተማ አስተዳደር ማስረከቡ ተገለጸ።
የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከመንግስት ጎን በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
የጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኮሬ ባዌ መጽሀፍት እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ርክክብ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት በአካባቢው በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ችግሮችን ያሳሰባቸው የአካባቢው ተወላጆች ጋበር የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል።
ድርጅቱ በዋናነት አላማ አድርጎ የተቋቋመው በእዣ ወረዳ ያሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን መንግስት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የአካባቢው ህብረተሰብ በማስተባበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ኮሬ ገለጻ በወረዳው ከ7-12ኛ ክፍል ለሚማሩ ልጃገረዶች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍት እንዲሁም ከ9-12 ክፍል ላሉ ተማሪዎች የማጣቀሻ መጽሀፍት ለእዣ ወረዳ እና ለአገና ከተማ አስተዳደር እንዳስረከበም ተናግረዋል።
ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የመጽሀፍ ድጋፍ እንዲሁም ቀልጣፋና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለአገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ለማሟላት ከመስራት ባለፈ በሌሎችም ዘርፎች ለመስራት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ድርጅቱ ከወረዳው አመራርና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ድርጅቱ በሚያከናውናቸው ስራዎች ህብረተሰቡና አመራሩ እያደረጉት ያለው ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ጋበር እያደረጋቸው ያሉ መሰል ስራዎች አርዓያነት ያላቸው ተግባራት በመሆናቸው የጉራጌ ተወላጆች በሁሉም አካባቢዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት በመመስረት በአካባቢያቸው የሚስተዋሉ የልማት ስራዎች ክፍተት ለመሟላት መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ምናሴ እንዳሉት 3 ሺህ 386 የሚሆኑ ማጣቀሻና የመማሪያ መጽሀፍ፣ 3286 የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በዋጋ ሲተመን 5 ሚሊዮን 326 ሺህ 437 ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል።
ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ ከማድረጉ ጎን ለጎን በወረዳውና በከተማው በሚገኙ በ7 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎችና በአገና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ትምህርታቸው ለሚከታተሉ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል።
ጋበር ከ1-6ኛ ክፍል በወረዳው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ 15 ሺህ 420 የመማሪያና የመምህር አጋዥ መጽሀፍት ለማቅረብ መጽሀፍቱ ህትመት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ለእነዚህ መጽሀፍት 4 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ያነሱት ስራ አስኪያጁ ከሚቀጥሉት ጊዜያት ጀምሮ ስርጭቱ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ጋበር እያካናወናቸው ያሉ ስራዎች ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የጋበር የቦርድ አባል ዶክተር እንዳለጌታ ከበደ ጋበር የማህበረሰቡን ችግሮችን በመገንዘንብ እየሰራ ያለው ተግባር ሌሎችም ድርጅቶች በዞኑ መሰል ስራዎች በመስራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ዶክተር እንዳለ ጌታ አክለውም እንደ ሀገር የወረደው ውጤት ተረድተው ተማሪዎች የተደረገላቸው ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ድርጅቱ በወረዳው ያለው የመጽሀፍ እጥረት በመገንዘብ ከአካባቢው ተወላጆችን ድጋፍ በማሰባሰብ የመማሪያና አጋዥ መጽሀፍት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
የእዣ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብዛ በበኩላቸው በወረዳው ያለው የመጽሀፍ እጥረት ችግር ለመፍታት ጋበር ድጋፍ ያደረገላቸው የመማሪያና ማጣቀሻ ብሎም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ መረከባቸውን ገልጸው እነዚህም በቀጣይ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች ተደራሽ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
የተደረገው ድጋፍ በአሁን ወቅት የወረደው የተማሪዎች ውጤት ከፍ እንዲል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል።
የወረዳ አስተዳደር ጋበር በወረዳው እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን እንደሚያግዝና በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ጋበር ሀገር ተረካቢ ዜጎች ለማፍራት እያደረገው ያለው አርአያነት ያለው ተግባር በዞኑና በሀገር ደረጃ ያሉ መሰል ድርጅቶች በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች በትምህርት ጥራት ላይ ያለው ችግር ለመቅረፍ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ተማሪ ዮርዳኖስ ይርጋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ለምለም ታሪኩና ዳንኤል ፉጀ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።
ተማሪዎቹ በጋራ በሰጡት አስተያየት ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ባደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ጠቁመው ይህም ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ተግተው እንደሚማሩ ገልጸዋል።
በተለይም በትምህርት ቤቶች የመጽሀፍ እጥረት እንዳለ ገልጸው ጋበር ያደረገው ድጋፍ ችግሩን እንዲቀንስ ከማድረጉም ባለፈ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ያደርጋል ነው ያሉት።
በንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩና የሚያቋሩጡ ተማሪዎች እንደነበሩ ጠቁመው ይህም ሴት ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸው በመከታተል ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።






