የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት በመስጠትና አሰራሩን በማዘመን የሆስፒታሉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ የቋንጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

*======================*

የካቲት 2/2016 ዓ.ም [ቋንጤ]
ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት በመስጠትና አሰራሩን በማዘመን የሆስፒታሉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ የቋንጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡
ሆስፒታሉ የ2016 ዓ.ም ሁለተኛ ሩብ ዓመት የማህበረሰብና የቦርድ ውይይትም አካሂዷል፡፡
የቋንጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገንብቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አጭር እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በፈጣን ለውጥ ውስጥ እያለፈ በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የውስጥ አሰራርን አዘምኖ ከመሄድ ጋር ይበል የሚያሰኝ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ያለ ተቋም ነው፡፡
ሆስፒታሉ በትናንትናው እለት ከአራት ቀበሌ ከተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኸይረዲንና የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ አ/ላዚዝ ፋዲል እንዲሁም የሆስፒታሉ ሙሉ ማኔጅመንት በተገኙበት በሆስፒታሉ የውስጥ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጡ ዙርያ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል፡፡
በእለቱም ከተሳታፊዎች በርካታ ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችና በቀጣይ ቢታረሙ ያሉዋቸውን ጉድለቶች ያነሱ ሲሆን የመዳኒት እጥረት፣ የአምቡላንስ ተደራሽነት ችግር፣ የጥቂት ባለሙያዎች የስነ-ምግባር ችግርና የጥርስ ሀኪም ያለመኖር የሚሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
በዛሬው የቦርድ ስብሰባ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪና የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል እንዳሉት የጤና ተቋማት ከህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ባልተናነሰ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በተለይም የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀቶችን በማጠናከር የቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ሰብሳቢው አክለውም ሆስፒታሉ አሁን ያለበትን ደረጃ በማድነቅ በቀጣይ ራሱን በተለያዩ የህክምና መሳሪያዎችና የሰው ሃይል በማደራጀት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ደረጃውን ከፍ ለማድረግ መጣር እንዳለበት ጠቁመው በዚህም የዞኑ መንግስት አቅሙ በፈቀደ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በበኩላቸው ሆስፒታሉ አሁን ላይ ያሉበትን በርካታ ችግሮች ተጋፍጦ ለህዝቡ አገልግሎት እየሰጠበት ያለው መንገድ አድንቀው በቀጣይም በስሩ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችንና ጤና ኬላዎችን ደግፎ በማብቃት መጓዝ አለበት ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ በየጊዜው ከህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን እየፈታ የመጣበት መንገድና አሰራሩን በማዘመን የህብረተሰቡን ርካታ ከመጨመር አንፃር ያመጣው ፈጣን ለውጥ በቀጣይ ደረጃውን ለማሻሻል በምናደርገው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ደግሞ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በህሩ ኸይረዲን ናቸው፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም ወረዳው ሆስፒታሉ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ የሆነ የበጀት ድጋፍ ሲያደርግ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው በዘንድሮ አመትም ለነዳጅና መዳኒት ግዢ፣ ለተሽከርካሪና ማሽነሪ ጥገና እንዲሁም ለመዳኒት ክፍል ቁሳቁስ ማሟያ በጥቅሉ ከ2.4 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ግርማ በበኩላቸው ተቋሙ ምንም እንኳን በርካታ ውስጣዊ ችግሮች ቢኖርበትም የገጠሙትን ተግዳሮቶች በመቋቋም በህክምና ዘርፉም ሆነ በስሩ የሚገኙ የጤና ተቋማትን በመደገፉ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተለይ የእናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ፣ ተኝቶ ህክምና፣ በሪፈር ለሚመጡ ታማሚዎችና ለድንገተኛ ክፍል ታካሚዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተቋሙ ካለበት ከፍተኛ የሆነ የባለሙያዎችና የበጀት እጥረት፣ የህክምና ማሽነሪዎች ብልሽት (ማይክሮስኮፖች፣ ሲቢሲ ማሽን፣ ፍሪጆች፣የአንስቴዥያ ማሽን)፣ የመብራት መቆራረጥ፣ በኢትዮጵያ መዳኒት አቅርቦት ድርጅት (EPSA) የሚፈለጉ መዳኒቶች በብዛት ያለመገኘት ችግሮች ሆስፒታሉን እየተፈታተኑት ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የቦርዱ አባላት በህዝብ ውይይትና በቦርዱ ውይይት የተነሱ ችግሮችን በየደረጃው ያለ ባለድርሻ አካል ተቀናጅቶ በመስራት በፍጥነት እንዲቀረፉ አቅጣጫ ማስቀመጡንና የ2016 ዓ.ም የ2ኛ ግማሽ አመት እቅድ ላይ ተወያይቶ ማፅደቁን የዘገበው የወረዳው መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት ነው፡፡