
የጉድድየ ፏፏቴ
የጉድድየ ፏፏቴ በጉራጌ ዞን በእዣ ወረዳ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች አንዱ ሲሆን የሚገኘው በእዣ ወረዳ ዌራደባነ ቀበሌ ከዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ 48 ኪ.ሜ ከወረዳው ዋና ከተማ አገና 6 ኪ.ሜ ከዋናው መንገድ በ3ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከዋናው መንገድ ወደ ደቡብ ገባ ብሎ ይገኛል፡፡ ይህ ፏፏቴ ከሌሎች በወረዳችን ካሉ በርካታ ፏፏቴዎች ለየት የሚያደርገው ውሃው የሚፈሰው ከትልቅ ክብ የሆነ የድንጋይ ጉድጓድ ገብቶ የሚፈስ ስለሆነ ልዩ ውበትና ድምቀት ይሰጠዋል የፏፏቴው ርዝመት ቢያንስ እስከ 5 ሜትር ርዝመትና እስከ 7 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ሌላው በፏፏቴው አከባቢ በርካታ የሆኑ የእፅዋት፣ የእንስሳትና የአዕዋፋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ በአከባቢው የሚገኙ የእፅዋትና የአዕዋፋት ድምፅ ልዩና መንፈስን የሚያድስ ተሰጥኦ አለው፡፡ በዙሪያው ካሉት እፅዋቶች መካከል የፅድ፣ የቀርከሀ፣ የባህር ዛፍ፣የግራር ዛፍ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እናም ይህ ውብና ማራኪ ቦታ መጥታችሁ እንድትጎበኙ ስንል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡


የገነማር ፏፏቴ
ገነማር ፏፏቴ በማእከላዊ ኢትዮጽያ ክልል በጉራጌ ዞን በእዣ ወረዳ በቆጠር ቀበሌ ልዩ ስሙ የበሰራር በሚባል የልማት ቡድን የሚገኝ ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ ማለትም ከወልቂጤ 54 ኪ.ሜ ከወረዳው ዋና ከተማ አገና በ12 ኪ.ሜ እንዲሁም ከዋናው ፒስታ መንገድ ቆጠር በ4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ገባ ብሎ የሚገኝ ልዩና ድንቅ ፏፏቴ ነው፡፡ ይህንን ፏፏቴ በአራቱም አቅጣጫ የሚያዋስኑ ቀበሌዎች መሀል ላይ የሚገኝ ሲሆን አዋሳኝ በምስራቅ ሻመነ ቀበሌ በምዕራብ ዋሳማር ቀበሌ በሰሜን ቆጠር ቀበሌ እና በደቡብ የዋራውያ ልማት ቡድን መሀከል ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንን ድንቅ ፏፏቴ ቁመቱ ከአንድ መቶ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሲሆን የፏፏቴውም የውሀ መጠን በጣም ከፍተኛ እና የተለያዩ የሁለት ወንዞች ድምር ውጤት ነው፡፡ ከፏፏቴው ጋር አብረው የሚገኙበት የተለያዩ የዱር እንስሶች እና የእፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ጅብ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛ እና ሌሎችም የዱር እንስሶች ይገኙበታል፡፡ ከእፅዋት ዝርያዎች መካከል የቀርከሀ፣ የተለያዩ የጽድ ዝርያዎች፣ የባህርዛፍ እና ሌሎችም የእፅዋት አይነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እናም ይህ ድንቅ እና ውብ የሆነ የተለያዩ ተፈጥሮዎችን አዋህዶ የያዘ ስፍራ እንድትጎበኙ ግብዣችን ነው፡፡






