





በዞኑ በንቅናቄ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች በዘላቂነት ለማስቀጠል አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል፦የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ወቅታዊ የንቅናቄ ተግባራት አፈፃፀም የዞን፣የወረዳና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በግምገማው ወቅት እንዳሉት በዞኑ በንቅናቄ እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች፣ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልፀው፣ በዘላቂነት ለማስቀጠል አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ግብርና የድህነታችን መውጫ፣ የኢኮኖሚያችን ማረጋገጫ በመሆኑ በአሁን ሰዓት ያሉን የመስኖ አቅም በአግባቡ በመጠቀም ግብርናውን ማዘመንና የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል።
አቶ ላጫ አክለውም የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ኢኒሼቲቮች የህብረተሰቡ መሰረታዊ ጥያቄ የሚፈቱ እንደመሆናቸው መጠን የኮሪደር ልማት ስራ የህብረተሰቡ የስራ ባህልን የቀየረ በመሆኑ የተጀማመሩ አመርቂ ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል።
በተለይ የከተማ የኮሪደር ስራ ቤቶቹ ከፈረሱ በኋላ ጊዜ ሳይሰጣቸው በአፋጣኝ ሰርቶ መጨረስ እንደሚገባና የዞናችን ከተሞች ደግሞ የጉራጌ ማህበረሰብ የሚመጥኑ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ጀፎረን ከገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ጋር በማስተሳሰር ጀፎረን ይዘቱን ጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ መክረዋል።
በቀጣይ ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ፣ ነባር የገበያ ማእከላት ወደ ዘመናዊ ገበያ ማእከልነት መቀየርና የወባን በሽታ በንቅናቄ በመምራት ወረርሽኙ በአፋጣኝ መከላከል እንደሚገባ አቶ ላጫ መመሪያ ሰጥተዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል በንቅናቄ እንዲሰሩ የወረዱ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸው ገልጸው በቀጣይ በዞናችን ያሉ የመልማት አቅሞችን በአግባቡ በመጠቀም ከዚም የበለጠ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
እነዚህ ስራዎች በውጤታማነት ለማከናወን አመራሩ በቁርጠኝነት ፣በታማኝነት፣ በኃላፊነት መስራትና ትግሉን ይበልጥ እንዲያጠናከር አስገንዝበዋል።
ስራዎች በጥራት ፣በፍጥነት ፣በስፋት እንዲሁም በፍትሀዊነትና በግልጸኝነት በመስራት የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
አቶ አለማየሁ አክለውም አመራሩ ነባራዊ ሁኔታን ማጥናት፣የህግ የበላይነት ማረጋገጥና የተሰጠው ተግባር በጥንቃቄ ሰርቶ ማስረከብ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የስራ ኃላፊዎች እንደተናገሩት ከድህነት ለመሻገር ግብርናው ላይ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ ገልጸው በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣በመስኖ ልማት ስራዎችና በሰብል አሰባሰብ ላይ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከተማና በገጠር የሚሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ህብረተሰቡ ያሳተፉ የውይይትና የሀብት አሰባሰብ ተግባራቶች እየተከናወኑ ሲሆን እነዚህም ለከተሞች ውበትን፣ የህብረሰቡን ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለሻ ቁልፍ ተግባር መሆኑ የገለፁት ሀሳብ ሰጪዎቹ ደረሰኝ የመቀበል ልምዳችን በማጎልበት የገቢ አቅማችን ማሳደግ ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት ተግባር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ገለጸው በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች የተጀማመሩ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች አጠናክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ጉራጌ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ







