የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት አዘጋጅነት የመስክ በዓል ተከብሯል

በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ ምርጥ ተግባራቶች በማስፋፋት የአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በትጋት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ ።

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት አዘጋጅነት የመስክ በዓል ተከብሯል ።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የግብርናው ሴክተር ዋና አላማ የግብርና ስነ-ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፡ ለግብርና ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማምረት ፡ የስራ እድል ፈጠራ ማስፋፋት ፡ ድህነትን ማሸነፍ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መምራት ይጠይቃል ።

በዘርፉ የሚጠበቅ ውጤት ለማሳካት የተነደፉት ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እውን ለማድረግ እንደ ወረዳው በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ዋና አስዳዳሪው ሆኖም በተፈለገው ልክ ውጤታማ ከማድረግ አንፃር አሁንም ጠንካራ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

በቀጣይ በዛሬው እለት በጉብኝቱ የታዩ አስተማሪ ተግባራቶች በሁሉም የቀበሌ አካባቢዎች በማስፋፋት የአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ በትጋት መሰራት እንደሚያስፈልግም አቶ ዘውዱ አሳስበዋል ።

የእዣ ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ መቻል ተሰማ በበኩላቸው የ2017 ምርት ዘመን እንደ ወዳው ግብርናው የሚገኝበት አፈፃፀም ደረጃ በመስክ ለመገምገምና የቀጣይ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥና ድክመቶችን ለማረምና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋት ይህ የመስክ በዓል መካሄዱንም ጠቁመዋል።

በጉብኝቱም በመኸር ከተሸፈነው 6435 ሄ/ር አመታዊ ሰብሎች ውስጥ በኩታገጠም የለማው የገብስ ማሳ በአንበሊ ቀበሌ ፡ የጤፍ ማሳ በሸህረሞ ቀበሌ ፡ በመኸር የለማ የነጭ ሽንኩርት ማሳ በቦዠባር ቀበሌ ፡ እንዲሁም የ30-40-30 ፕሮግራም የፍራፍሬ ልማት ስራዎች በየስራይ ቀበሌ የጉብኝቱ አካል መሆናቸውንም ሀላፊው ጨምረው ተናግረዋል ።

በዚህ ጉብኝትም በርካታ ልምዶች የተቀሰሙበት ሲሆን በቀጣይ ወቅታዊ የሆኑ የግብርና ስራዎች ለአብነት ፡ የሰብል አሰባሰብ ፡ የበጋ መስኖ ልማት ስራ ፡ የበልግ እርሻ ዝግጅት ፡ የዝርያ ማሻሻያ ስራ ፡ የተለያዩ የቡና ፡ የፍራፍሬ ፡ የደንና የመኖ ችግኞች እንክብካቤ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አቶ መቻል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተሳታፊዎቹም በሰጡት አስተያየትም በዛሬው በተመለከቱት የግብርና ልማት ስራዎች ከተሰራ እጅግ ውጤት ማምጣትና ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል በተጨባጭ ያዩበት እንደሆነ ገልፀው በቀጣይ በየአካቢአቸው ተሞክሮውን ለማስፋት ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በጉብኝቱም የወረዳው አመራሮች ፡ የወረዳና ቀበሌ ባለሙያዎች ፡ የቀበሌ ሊቀመናብርትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።