










=======ነቖ ወይንም የልጃገረዶች በዓል ቀን በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በጉየና የስዋ ቀበሌ የማስጀመሪያ ፕሮግራም እየተካሄደ ይገኛል።
ነቖ (ኧረቘ) በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ በጥር ወር ላይ ወይም ገና በዋለ እስከ 15ኛው ቀን ባሉት ጊዜያት በሴት ልጃገረዶች የሚዘወተር ባህላዊ የበዓል አይነት ነው።
በዓሉም ሴት ልጃገረዶች ነጻነታቸውን የሚያውጁበትና ደስታቸውን የሚገልጹበት በዓል ነው።
በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶች ተሰባስበው በየቤቱ እየዞሩ ልክ እንደ አበባዮሽ በአይነትና ገንዘብ ይሰበስባሉ፣ ሁሉም የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና ምግብ ከተዘጋጀ በኋላ ከአካባቢው በአንዷ ልጃገረድ ቤት በማደር የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት እየጨፈሩና እየበሉ ያድራሉ፡፡
የነቖ በዓል በጥር ወር የሚከበር ሲሆን ከታህሳስ ወር ጀምሮ ለበዓሉ የሚሆን ቅድመ ዝግጅት ተጀምሮ ክትፎ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ቦርዴና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦች ዝግጅቶች ይደረጋል። ልጃገረዶቹ ከሚያደርጉት ዝግጅት ባለፈ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ወላጆቻቸው አስፈላጊውን እገዛ ያደርጉላቸዋል።
ይህ የልጃገረዶች በዓል በዞኑ በየአመቱ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝና የዘንድሮ የነቖ የልጃገረዶች በዓል ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ድረስ በልዩ ድምቀት እየተከበረ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በበዓሉም የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ፣ የወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተሾመ ስራኒ፣ የወረዳው ባህል ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የሺነሽ ተካና ሌሎችም የዞንና የወረዳው የስራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።







