
**************************************
ከሚያራርቁ የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት አንድነትና ሰላማችን ማስከበር እንደሚገባን ተገለፀ ።
የእዣ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት በሀይማኖትና እምነት ጉዳዮች ለቀበሌ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላትና ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል ።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከቀድሞ ጀምሮ የነበሩትን የመከባበር ፡ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች ሰላም በማይፈልጉ አንዳንድ ሀይሎች እንዳይደበዝዙ በንቃት መሰራት ይገባል ።
ከሚያራርቁ የሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት አንድነትና ሰላማችን ማስከበር እንደሚገባን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም የሀይማኖት አባቶች ሃላፊነታቸው እጥፍ ድርብ መሆኑን በመገንዘብ አልፎ አልፎ በወረዳው የሚስተዋሉ የፅንፈኝነት እና የአክራሪነት እንዲሁም የተዛቡ አስተሳሰቦች ለማረም የጎላ ሚና መጫወት ይገባቸዋልም ብለዋል ።
ትብብርን ሳይሆን ፉክክክርን ማዕከል የሚያደርጉ ጉዳዮች መታረም አለባቸው ያሉት አቶ ዘውዱ በአንዳንድ ቤተ እምነት በሚስተዋሉ የአስተምሮ ችግሮች በፅኑ በመታገልና በማውገዝ የተጀመረውን የሰላም ሁኔታ እንዲዘልቅና እንዲፀና የሀይማኖት አባቶች ከመንግስት ጋር በመተባበር የበኩላችንን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የእዣ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ሀላፊ ደመቀ ሀብቴ በበኩላቸው የሀይማኖት ተቋማት ትውልድን በመቅረፅ ረገድ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን በዚህም የተገነባ ትውልድ ለወረዳው ብሎም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በወረዳው ለረጅም ጊዜ የቆየውን የማህበረሰቡ ሰላምና አንድነት በላቀ መልኩ እንዲቀጥል ርብርብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው ያሉት አቶ ደመቀ በወረዳ አንዳንድ ጥቂት የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ከጥንት ጀምሮ የቆየውን የማህበረሰቡ አንድነትና ሰላም እንዳያዛቡ በተረጋጋ ሁኔታና በጥልቀት በመገንዘብ የሀይማኖት አባቶች ያላቸውን ትልቅ አደራና ሀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የፅ/ቤቱ ባለሙያ የሆኑት አቶ ቶፊቅ ሺፋ በወረዳው በሀይማኖትና እምነት ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን የእምነት ተቋማት ከየትኛውም ፖለቲካ ሰለባ እንዳይሆኑ ነቅቶ በመጠበቅ የራሳቸውን አስተምሮት ብቻ ላይ በማተኮር ለወረዳው ብሎም ለሀገር ሰላምና ለህዝቡ አንድነት እንዲሁም መፈቃቀር ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም በሰነዱ አመላክተዋል ።
በእለቱም የተሳተፉት የሀይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየትም በየቤተ እምነቱ ያሉት የሀይማኖት አባቶች አንዳንድ ችግሮች ሲኖሩ መግባባት እንዲፈጠር የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎች አክለውም በተለይም የሀይማኖት አባቶች በየቤተ እምነታቸው ለምዕመናኑ በሰላምና በአብሮነት ላይ አስተምሮት ላይ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል ።
በቀጣይም ለወረዳው ብሎም ለሀገር ፍፁም ሰላምና አብሮነት ላይ በመንግስት ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸው እንደሚወጡም በአስተያየታቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው ።






