






እያደገ ለመጣው የህዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ እየተካሔደ ነው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በንቅናቄ መድረኩ በሰጡት የስራ መመሪያ እንደገለጹት እያደገ ለመጣው የህዝብ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ይገባል ብለዋል።
ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ከችግር ለመውጣት በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች የሚሰበሰበውን ገቢ በተገቢው መንገድ እንዲሰበሰብ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አመራሩ በገቢ አሰባሰብ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳደግ ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።።
አዳዲስ ሀሳቦችን እና አሰራሮችን መዘርጋት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የገቢ መሰረትን ማዘመን ተገቢ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ገቢን አሟጦ መጠቀም እና መሰብሰብ የፋይናንስ ዘርፉን ስኬታማ እንደሚያደርገውም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
ከተለያዩ መንገዶች የሚገኘውን ገንዘብ መቆጠብ እና ሀብትን በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አሰራርን በማዘመን የሀብት ብክነትን መከላከል እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም በየደረጃው የሚገኘው አመራር የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
እያንዳንዱ መዋቅር እራሱን መቻል አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ገቢን መሰብሰብ፣ወጪን መቆጠብ፣ብክነትን ማስወገድ፣ቅንጅት እና ጠንካራ አመራር መስጠት ይገባል ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ እንደገለጹት በቀጣይ ሶስት ዓመታት ከእዳ ነጻ የሆነ ክልል ለመገንባት ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፋይናንስ ዘርፉ በግል እና በተቋማዊ አውድ ለውሳኔ አሰጣጥ፣ለእቅድ እና ስትራቴጂ ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር መሀመድ ጠቁመዋል።
የፋይናንሻል መረጋጋትን እድገት እና ዘላቂነትን ለማምጣት መሰረታዊ መርሆዎች እና አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ወሳኝ ስለመሆኑ የተናገሩት ኃላፊው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመጣው የኢኮኖሚ ከባቢ ላይ ያለውን አበርክቶም አብራርተዋል።
የፋይናንስ ቢሮ ባሳለፍነው አመት የክልሉን መንግስት በጀት ዝግጅት እና የአስተዳደር ስርዓት በማጠናከር ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል፣አመዳደብ እና የበጀት አጠቃቀምን ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኑን ዶ/ር መሐመድ በአብነት ጠቅሰዋል።
የመንግስት ሂሳብ አያያዝ እና ሪፖርት ላይ ከወቅታዊነት እና ጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች መስተዋላቸውን የተናገሩት ኃላፊው በ2016 ዓም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በህግ በተቀመጠው አግባብ ብቻ ሀብትን በቁጠባ የመጠቀም ባህልን በማዳበር ወጪን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራም ዶ/ር መሐመድ አብራርተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም እንደገለጹት በ2016 በጀት አመት በፋይናንስ ሴክተሩ ያጋጠሙ ችግሮችን በመሻገር የመንግስት ተቋማት በተሟላ መንገድ ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
በሁለት ዙር የመቶ ቀናት እቅድ በማዘጋጀት መደበኛ ስራዎችን ለመምራት ጥረት መደረጉን የተናገሩት ወ/ሮ ዘይቱና ከዚህ ቀደም የነበሩ እዳዎችን በማስተዳደር ረገድ የተከናወኑ ስራዎችን ኃላፊዋ በንግግራቸው ጠቅሰዋ።
የክልሉ መንግስት የነበሩ እዳዎችን ወደ ምንዳ ለማሸጋገር ጠንካራ የፖለቲካ አመራር ስርዓት በመዘርጋት የላቀ ድጋፍ ማድረጉን ኃላፊዋ አስረድተዋል።
ሴክተሩ በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣን እና ተግባር በአግባቡ ለማስፈጸም እንዲሁም የሀብት አስተዳደር ስርዓቱ ቀልጣፋ፣ወጪ ቆጣቢ እና ውጤታማ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ወ/ሮ ዘይቱና ጠቁመዋል።
መረጃው የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ነው።






