







የካቲት 23/2017 ዓ.ም
የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው። የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ ዶ/ር
ሚንስትሯና ልዑካን ቡድናቸው በጉራጌ ዞን በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ምልከታ አድርገዋል።
የኢፌድሪ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው።
ሚኒስትሯ በወልቂጤ ጤና ጣቢያ የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ ፣የድህረ ወሊድ፣ የህክምና፣የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንዲሁም በጤና ጣቢያው በተለያዩ የስራ ክፍሎች እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ምልከታ አድርገዋል።
መንግስት በየደረጃው ህብረተሰቡን የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ መስሪያ ቤታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀ ይደረጋልም ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በጉመር ወረዳ የእንጀፎ መሰረታዊ ጤና ኬላ የአገልግሎት አሰጣጥና የሞዴል ቤተሰብ መንደር ምልከታ ያደረጉ ሲሆን በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውም አንስተዋል።
ፍትሃዊ የጤና ተቋማት ተደራሽ በማድረግ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ ለማፍራት በዘርፉ ይበልጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የወልቂጤ አጠቃላይ ሆስፒታል በክልሉ መንግስት ግንባታው መጀመሩን አንስተው ይህም ለብዙ ሆስፒታሎች ሞዴል የሚሆን በተለየ ስታንዳርድ እየተገነባ ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ በወቅቱ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ በህብረተሰቡ ዘንድ በየጊዜው ጥያቄ ሲያስነሳ መቆየተን አንስተዋል።
አጠቃላይ ሆስፒታሉ የህዝብና የመንግስት ሀብት ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው ለዚህም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለታለመለት አላማ እንዲውል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የህንጻው ተቋራጭ አቶ ዮሀንስ ሀይሌ የሆስፒታሉ ግንባታ የፊዚካል አፈጻጸሙ 86 ከመቶ መድረሱን አንስተው ይህም በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።
የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከድር መንግስት የህብረተሰቡን ጤና ለማበልጸግ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጥራት ለማሻሻልና ቀልጣፋና ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለመስጠት በዘርፉ የነበሩ ችግሮች ለመፍታት አዲስ የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ገብቷል።
በወረዳው በዘርፉ አበረታች ስራ መሰራቱንም ጠቁመው የተጀመረው አዲሱ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በጉመር ወረዳ አግኝተን ያነጋገርናቸው የእንጀፎ ቀበሌ ነዋሪዎች እንዳሉት የቤታቸው ንጽህና በመጠበቃቸው፣ ሽንት ቤት በየቤታቸው በመገንባታቸውና ቆሻሻ በተገቢው በማስወገዳቸው ጤንነታቸው እንደተጠበቀ አንስተዋል።
መሰረታዊ ጤና ኬላው በአቅራቢያቸው በመኖሩ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ትምህርት እንደሚሰጣቸውና ይህም ሁሉም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ተናግረዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው አመላክተዋል።
በመጨረሻም ለክብርት መቅደስ ዳባ ዶ/ርና ሉዑካን ቡድናቸው ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።







