የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

የጉራጌ ማህበረሰብ ውብ ባህላዊ ጎጆ ቤት !!

የጉራጌ ማህበረሰብ ውብ ባህላዊ ጎጆ ቤት !!
የጉራጌ ማህበረሰብ እጅግ የሚደነቅ የበርካታ ባህላዊ ዕሴቶች ባለቤት ነዉ፡፡
ከዚህ ዉስጥ ባህላዊ የሳር ቤት “ጎጆ ቤት” አሰራር አንዱ ነዉ፡፡

በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ባህላዊ የቤትና የመንደር አመሰራረት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ የሚከናወን ተግባር ነው ።

አባቶች ዘመናዊ የምህንድስና ትምህርት ምን እንደሆነ ሳያዉቁ የሳር ቤት አወቃቀርና የመንደር አመሰራረት እንዲሁም የቤት አያያዝና አጋጌጥ እጅግ የሚገርም ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም ፡፡

የጉራጌ ባህላዊ ቤት አንዲት ምስማር ወይም የፋብሪካ ውጤት ሳይገባበት ተሰርቶ ከ100 እስከ 120 ዓመት ምንም ሳይሆን አገልግሎት መስጠት እንደሚችል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን የጎጆ ቤቱ ይዘት ሳይረሳ እጅግ በዘመነ መልኩ ሲሰራ እናስተውላለን ።ይህም የበለጠ ረጅም ጊዜ እንዲያስቆጥር እድል የሚፈጥርም ነው ።

የጉራጌ ባህላዊ ቤቶች በሶስት ደረጃ የሚከፈሉ ሲሆን እነሱም ጉየ “ትልቅ ቤት” ፣ ኸራር “እልፍኝ ቤት” እና ዘገር “የሙሽሮች ቤት” በመባል ይታወቃሉ፡፡

የውስጡን ገጽታ ስንመለከት የጉራጌ ባለሙያዎች ተጠበዉና ተጨንቀዉ በሚሰሩዓቸዉ የእደ ጥበብ ዉጤቶች የሚያሽቆጠቁጡት ሲሆን በተለይም ከስንደዶ ፡ ከሸክላ፣ ከእንጨት፣ እንሰት ዉጤቶች “ቃጫና ገመድ” በመጠቀም እንዲሁም ከእንስሳት ተረፈ ምርቶች ማለትም ከቆዳ፣ ከቀንድ፣ ከጭራና ከመሳሰሉት የተዘጋጁ ቁሳቁሶች በአግባቡና በሚያምር መልኩ ተደርድረዉ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ጥቅም ላይ ይዉላሉ፡፡

ባህላዊ ቤት ሲገነባ፤ በአንድ ጀንበር ታስቦ የሚከናወን ተግባር ሳይሆን፤ ቤት የሚሰራዉ አባወራ ለቤቱ መስሪያ የሚሆኑ ቁሳቁስ ለማሰባሰብ ጊዜ ወስዶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ የአካባቢው ህብረተሰብ ደግሞ አንድ አባወራ ቤት ሲሰራ ሌላ ዳር ሆኖ መመልከት የማይታሰብና እንደ ነዉር የሚታይ ስለሆነ ሁሉም ተረባርበዉ ቤቱን በጋራ የመስራት ባህል የተለመደ ዕሴት ነዉ፡፡