
=====================
“ጋበር” የበጎ አድራጎት ድርጅት ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ለ6 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየውን የመምህራን ስልጠና በዛሬው እለት ተጠናቋል ።
የእዣ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለፁት ይህ ስልጠና እንደ ሀገር የገጠመውን ከፍተኛ የሆነ የተማሪዎች ውጤትና ስነ -ምግባር ስብራት እንደ ወረዳው ለማካካስ ሚና የጎላ መሆኑን አላማ ተደርጎ የተሰጠ ነው ብለዋል ።
አብዛኛው በሚባል ደረጃ የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር እንዲሻሻል የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው መምህር ነው ያሉት ም/አስተዳዳሪው እንደ ወረዳው ዘላቂነት ባለው መልኩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ይህንኑ በመገንዘብ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ለመምህራን የነበራቸውን እውቀት በሚያሻሻል መልኩ ያለመ ስልጠና ሰጥቷል ብለዋል።
ለዚህም ስልጠና ፅ/ቤት መሰረታዊ የሆኑ የትምህርት አይነቶች በመለየት በተለይም በቀጣይ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል እንዲያስችል ሰፊ የሆነ ስራ ተሰርቷል ያሉት አቶ ተጠምቀ ይህንን የተሰጠው ስልጠና መምህራኑ በአደራ መልክ መወጣት አለባቸው ብለዋል ።
በተለይም መምህራኖች ከአዲሱ መፅሀፍ ጋር ያላቸው መስተጋብር እንዲሻሻል በተለያየ መልኩ መዘጋጀት አለባቸው ያሉት ም/አስተዳዳሪው የአንዱን እውቀት ለሌላው በማካፈልና ያልገባንን ከገባው በመጠየቅ እንደ ወረዳው በዘንድሮ አመት በተወሰነ ደረጃ ውጤት በማሻሻል ለሌሎችም አካባቢዎች ተሞክሮ እንድንሆን ከመምህራን ብዙ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
ለዚህ ስልጠና መሳካት ከፍተኛ ድርሻ የተጫወቱት ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ፡ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፡ የወረዳው መንግስት ፡ የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እና ለሰልጣኝ መምህራን አቶ ተጠምቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተወካይ ረ/ፕሮፌሰር አበበ ባበኬር በበኩላቸው አንድ ሀገር ምትገነባው በእውቀትና ስነ-ምግባር የተገነባ ትውልድ ስታፈራ በመሆኑ በትውልድ ላይ መስራት አማራጭ የሌለው ነው ብለዋል።
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በተወላጅ ባለሀብቶችና ማህበረሰቡ የተመሰረተ ጋበር በጎ አድራጎት ድርጅት እያደረገው ያለው ትውልድ የማነፅ ስራ እንደ ሀገር ተሞክሮ የሚሆን አርዕያነት ያለው ተግባር ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲም እያደረገውን ያለው ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥልም ነው ብለዋል።
የጋበር በጎ አድራጎት ማህበር የክትትልና ግምገማ ሀላፊ ዶ/ር ደርብ ወ/ዮሀንስ በበኩላቸው ጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት በእዣ ወረዳ ያሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ከወረዳው መንግስት ጋር በመተባበር በወረዳው ተወላጆች የተቋቋመ ነው ብለዋል።
የጋበር አላማ ሰፊ በመሆኑ በተመሰረተበት አንድ አመት ገደማ እጅግ በርካታ ስራዎች መስራት ችሏል ያሉት ዶ/ር ደርብ በተለይም በትምህርት ላይ በርካታ የሆነ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ ዙር በተሰጠው ስልጠና ከወረዳው ትምህርት ፅ/ቤት ጋር በመተባበር ከ9 – 12ኛ እንግሊዝኛ ፡ ሂሳብ ፡ ፊዚክስ ፡ ኬሚስትሪና ኢኮኖሚክስ የሚያስተምሩ መምህራን እንዲሁም ከ7-8ኛ የሚያስተምሩ እንግሊዝኛና ሂሳብ መምህራን ስልጠናው ያገኙ ሲሆን በአጠቃላይ 152 መምህራን በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ 2ኛ ዲግሪና 3ኛ ዲግሪ ያላቸው መመህራን ስልጠናው በአግባቡ መከታተላቸውን አብራርተዋል።
በስጠናው የተካፈሉት መምህራኖች በሰጡት አስተያየትም ስልጠናው በራሳቸው ብሎም በተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እጅግ አስተማሪ ስልጠና በመሆኑ በቀጣይም በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት እንደ ወረዳ ለማምጣት የታሰበውን ውጤት እንዲመጣ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል ።
በስልጠናው መጨረሻም ለሰልጣኝ መምህራን የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቶአቸዋል ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።






