የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

ለእናቶች ፈጥኖ ደራሽ ተሽከርካሪ

============================

ለእናቶች ፈጥኖ ደራሽ ተሽከርካሪ
እናቶች በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ የሚደርስባቸው ችግር ስመለከት እረፍት ነስቶኝ ነበር። ወጣት የፈጠራ ባለቤት ተማሪ አብድልሀፊዝ ጸጋዬ
የጉራጌ ማህበረሰብ በርካታ የስራ ፈጠራ ልምድ እና ባህል ያለው ህዝብ በመሆኑ የስራ ፈጠራን ከማንም አስቀድሞ የተገነዘበ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ይህን ትልቅ ተግባር በትውልድ ቅብብሎሽ የቴክኖሎጂው ዘመን ላይ እንገኛለን።
በጉራጌ ዞንም ወቅቱን የዋጁ ጠበብት የፈጠራ ባለሙያዎች መፍለቂያ እየሆነ መሆኑ በዞኑና በክልሉ በተዘጋጁ ውድድሮች በግንባር ቀደምትነት አልፈው አሁንም በፌደራል ደረጃ ተደግፈው እየሰሩ መሆናቸው እና በተጨማሪም የፈጠራ ወጣቱ ኢዘዲን ካሚልን ማንሳት በቂ ማስረጃ ይሆናል።
ከእነዚህ በዞኑ ካሉ የፈጠራ ባለቤቶች ተማሪ አብድልሀፊዝን ለማንሳት ሞከረን። ተማሪው በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ የአንዝሬ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነው።
ተማሪ አብድልሀፊዝ እንደሚለው ከልጅነቴ ጀምሮ ከጓደኞቼ ሁኜ ስጫወት እንኳን ቁሳቁሶችን መገጣጠምና አዳዲስ ነገሮች ከመስራት እጄ አይቦዝንም ነበር።
ይህንን እንደ ልማድ ሆኖ በትምህርት ቤቴ እንዲሁም በአካባቢዬ የወዳደቁ ቁሳቁሶችን መሰብሰብ እና መገጣጠም የወትሮ ስራዮ አድርጌዋለሁ።
በተለይ እናቴ ቤት ውስጥ ስራዎች በቀላል መስራት ስትችል ብዙ ጉልበት እና ጊዜ ሲፈጅባት ስመለከት ለዚህ ችግር መፍትሄ ምን ይሁን? ብሎ ጭንቅላቴ አብዝቶ ያስባል።
በአካባቢዬ ምቹ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ከባድ ስራ መስራት፣እረጅም ጉዞ መሄድ፣ብዙ ገንዘብ ማውጣት የተለመደ ነው የሚለው ተማሪ አብድልሀፊዝ እነዚህ የማህበረሰቡ ችግር በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቼ ህብረተሰቡን ሲደሰት ለማየት ከትምህርቴ ጎን ለጎን ከፈጠራ ስራ ዝምድና ጀመርኩ ።
ከዚህ በፊት ውሃ መምጠጫ፣አይሮፕላን እና በሪሞት የሚሰራ መኪና ሰርቼ ለተለያዩ የፈጠራ ውድድሮች አቅርቤአለሁ ነው ያለው።
በአካባቢው የትራንስፖርት ችግር በመኖሩ ህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰው ጫና በጣም ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ በተለይ እናቶች ሲወልዱ በቃሬዛ ተሸክሞ መውሰድ ህይወታቸው እስከማጣት ሊያደርሳቸው ይችላል።
በተጨማሪም እናቶች ወደ ገበያ ሲሄዱ እና ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ወገባቸው ላይ የሚሸከሙት ሸክም ደግሞ እጅግ ከባድና ለጤናም የማይመከር ተግባር ነው።
እንደ አብድለሀፊዝ ገለጻ እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚከሰቱት መኪና ባለመኖሩ በመሆኑ እኔ ደግሞ በተለይ እናቶች በትራንስፖርት እጥረት የሚደርስባቸው ችግር ለመቅረፍ በጸሀይ ሶላር የሚሰራ መኪና መስራት እንዳቻለ አስታውቋል።
በሶላር መስራቱ ደግሞ የነዳጅ ችግር የሚቀርፍና ወጪ ቆጣቢ ያደርገዋል ያለው የፈጠራ ተማሪው መኪናው በአካባቢው ካሉ ቁሳቁሶች ተገጣጥሞ የተሰራ መሆኑን አስገንዝቧል።
ይህ የሰራው መኪና ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያና የዞኑ ትምህርት መምሪያ ባዘጋጁት ዞናዊ የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ውድድር ላይ በዞኑ በተማሪዎች ምድብ 2ኛ ደረጃ በመውጣት ተሸላሚ መሆን እንደቻለ አውስቷል።
የተበረከተለት የማበረታቻ ሽልማት ደስ ተሰኝቷል፤ ህልሙንም እውን ለማድረግ የሞራል ስንቅ እንደሚሆነው ስሜቱን አጋርቶናል።
በቀጣይም በክልል እና በፌደራል በሚዘጋጁ የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ውድድር ለመሳተፍ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለምታደርገው ጉዞ የበኩሌን እወጣለሁ ነው ያለው።
በቀጣይ ደግሞ ይህ የሰራሁት የፈጠራ ስራ ይበልጥ እያዳበርኩት ነው ያለ ሲሆን በተጨማሪም ድሮን እና የመብራት ተርባይን ለመስራት ጥረት እያደረኩ እገኛለሁ ብሏል ተማሪ አብድል ሀፊዝ።
ወደፊትም ፓይለንት የመሆን ህልም እንዳለው አጫውቶናል።
የፈጠራ ስራ ስሰራ የሀዋርያት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እና የቤተሰብ ድጋፍ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮልኛል።
ወጣቶች ዳግም የማያገኙትን ወርቃማ ጊዜያቸውን አልባሌ ስፍራ ከማሳለፍ ይልቅ ዘመኑ የዋጀውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ በማተኮር ተላምደን አብሮን ያለውን ችግሮቻችንን እንዲፈቱና መንግስትም ለዘርፉ እየሰጠ ያለው ትኩረት ማጠናከር እንደሚገባ ተማሪው ምክሩን ለግሷል።
እነዚህ የፈጠራ ስራዎቼ በቀጣይ ይበልጥ በማሻሻል የህብረተሰቡ ችግር ተቀርፎ የማየት ህልሜ ለማሳካት ሌት ተቀን እሰራለሁ ሲል ተማሪ አብድል ሀፊዝ አስታውቋል።
የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ