የእዣ ወረዳ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት

መስከረም 2016ዓ.ም የመስቀል በዓል ዝግጅትና አከባበር በጉራጌ በከፊሉ!!

መስከረም 2016ዓ.ም
የመስቀል በዓል ዝግጅትና አከባበር በጉራጌ በከፊሉ!!

የጉራጌ ብሔረሰብ በድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል ትልቁና ዋነኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡

የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ ትልቅ ነው ። ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሠቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸው የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች የተጣሉ ሠዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው፡፡

ወጣቶችና አዛውንት ደመራ ለማብራት በወጡበት በእድር ደንቦች በአካባቢ ልማት፣ በግብርናና ንግድ ስራዎች ላይ የሚመክሩበት፣ ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁት፣ ጎልማሶች ከአባቶች ኃላፊነት የሚረከቡት፣የወላድ ማህፀን የሚባረከው፣ ሟርተኞች የሚረገሙት በዚሁ በዓል ነው፡፡

ወላጆች ለበዓሉ የተዘጋጀን ሰንጋ ከፊታቸው አቁመው ሻኛውን በመዳሰስ ትውልዱን ይመርቃሉ /ይባርካሉ/፤ ለአገር ሰላምና ብልፅግና ፈጣሪያቸውን በፀሎት ይለምናሉ፡፡ በጐረቤት እና በአካባቢ ያለን ችግረኛ የሚያስቡበት፣ ለወለደች አራስ የሸሉዳ ስጋ፣ ለተገረዙ ልጆች ጭቅና ስጋ የሚሰጡበት በመስቀል በዓል ነው፡፡

በጥቅሉ የመስቀል በዓል አጀማመር መሰረት የሆነዉ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘት ሲሆን በአመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረዉ በ4ኛ ክፍለ ዘመን (327ዓ.ም) በንግስት እሌኒ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ለመስቀል በአል የሚደረግ ዝግጅት ብሔረሰብ ዘንድ ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ዝግጅቱም እንዲህ ከበድ ያለ ነዉ ፡፡
የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረዉ መስቀል በተከበረበት ዓመት በዓሉ እንደተጠናቀቀ ለሚቀጥለዉ አመት የመስቀል በዓል በማሰብ ነዉ ፡፡

በተለይ ከትዉልድ ቀዮአቸዉ ርቀዉ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ከቀን ሰራተኛዉ እስከ ደሞዝተኛዉ ከሱቅ በደረቴ እስከ ትልቁ ነጋዴ ለመስቀል በዓል ብለዉ የተለየ ገንዘብ በየጊዜዉ ጣል በማድረግ የሚያጠራቅሙት በበጋዉ ወራቶች ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እናቶችም ለመጪዉ መስቀል በዓል የቅቤ ዝግጅት የሚጀምሩ ገና በዓሉ እንደተጠናቀቀ ሲሆን ዓመቱ ሙሉ የማያቋርጥ የቅቤ ዉጆ/የቅቤ እቁብ /ማጠራቀም ለመስቀል በዓል ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጡት ትክክለኛ ማረጋገጫ ነዉ ፡፡መስቀል ሶስትና አራት ወራት ሲቀሩት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሔዳል፡፡

በዚህ ወቅት የስራ ክፍፍሉ በእድሜና በፆታ ተደላድሎ ለሁሉም እንደ አቅሙና ችሎታዉ ይሰጣል ፡፡ ወጣት ወንዶች ለመስቀል በዓል የሚሆን ባህርዛፍ በደቦ ቆርጠዉ በመፍለጥ የወይራ ዛፍ ጉቶ አዘጋጅተዉ ማደራረቅና ከደረቀም በኃላ ቤት አስገብቶ በቆጥ ላይ መደርደር ሲሆን ፣የአባዎራዎች ድርሻ የሚሆነዉ ለእርድ የሚሆኑ ከብቶች ማድለብና ማዘጋጀት ከቤትም ከሌለም አስቀድሞ ገዝቶ ማድለብ እንዲሁም በመስቀል ወቅት በቤት ዉሥጥ ያሉት ከብቶች የሚሰማሩበት ክልክል የሳር ቦታ መከለልና ለተወሰነ ቀናቶች የሚሆን ሳር አጭዶ ማቆየትና ለበዓሉ የሚሆኑ ቢላዎች መግዛት ማስሞረድ የመሳሰሉት ናቸዉ ፡፡

የወጣት ሴቶች የስራ ድርሻ ደግሞ ቤት ማሳመር የተለያ ቀለም ባለቸዉ አፈሮች ቤት መቀባት ሲሆን እማዎራዎች በቅድሚያ እንሰት ፍቀዉ ማዘጋጀት በደቦ አዲስ ጅባ መስራት ወይም መግዛት ያረጁና ያለቁ የቤት ቁሳቁሶች በአዲስ መለወጥ የመስቀል ሚጥሚጣ ከልጆች ጋር ወቅጦ ማዘጋጀት ፈሳሹ ተንጠፍጥፎ የወጣለት የበዓል ቅቤ በተለያ ቅመሞች አሽቶ ማንጠርና ለበዓሉ የሚሆኑ ባህላዊ መጠጦች ማዘጋጀት ዋና ዋና ተግባሮች ናቸዉ፡፡