
==================================
በእዣ ወረዳ በሁሉም ቅድመ አንደኛ ጣቢያዎች ህፃናት የአፈ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው በጉራጊኛ ቋንቋ እንደሚማሩ የወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት አስታወቀ ።
ፅ/ቤቱ እንደ ወረዳው የታተመው የጉራጊኛ ቋንቋ ደረጃ አንድና ሁለት የቅድመ አንደኛ የጉራጊኛ መፅሀፍ ከጣቢያ አመቻቾች ጋር የትውቅ ፕሮግራም አካሂዷል።
የእዣ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንደገለፁት የጉራጊኛ ቋንቋ በስርዓተ ትምህርት ተካቶ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መደረጉ ቋንቋውን ለማልማትና ለማጎልበት ጉልህ ድርሻ ከመኖሩም በተጨማሪ ህፃናት በቀላሉ ሀሳባቸው መግለፅ ያስችላቸዋልም ብለዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከህፃናት መብቶች አንድ ህፃናቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር እንዳለባቸው ተቀምጧል ያሉት አቶ ተጠምቀ በመሆኑም ህፃናቶች ከወዲሁ በቋንቋቸው ፊደል በመለየት በቀጣይ እንደ ዞኑ በአንድኛ ክፍል የሚጀመረውን የጉራጊኛ ትምህርት ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸውም ብለዋል።
ይህም የትውውቅ ፕሮግራም ለሁለተኛ ዙር የጉራጊኛ የፊደል ልየታ ገበታ ዙሪያ የሚሰጥ ስልጠና መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው ከዚህ ቀደም በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ያሰልጣኞች ስልጠና የሰለጠኑት ለሌሎች በማሰልጠን እንዲሁም በትምህርት ቤት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ጣቢያ ላይ መሰልጠን እንዳለባቸው በማመን ሁሉም የቅድመ አንደኛ አመቻቾች ስልጠናውን መውሰዳቸውንም አብራርተዋል ።
” ከጋበር ” በጎ አድራጎት ድርጅት ፡ ከማህበረሰቡ እንዲሁም ከመንግስት ጋር በመቀናጀት 370 የጉራጊኛ ቋንቋ ደረጃ አንድና ሁለት የቅድመ አንደኛ መፅሀፎች መታተማቸውን የጠቆሙት አቶ ተጠምቀ ለዚህም ህትመት ከ150 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸዋልም ብለዋል።
እንደ ወረዳው ቅድመ አንደኛ ላይ በደረጃ አንድና ሁለት እየተሰጠ ነው ያለውን ትምህርት በቀጣይም ሁሉም ጣቢያዎች በጉራጊኛ ቋንቋ ብቻ መሰጠት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀጧል ብለዋል ።
በመሆኑም አመቻቾች ይህንኑ በመገንዘብ በቂ ግንዛቤ ይዘው ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን እንዲማሩ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በእለቱም ስለ ጉራጊኛ ቋንቋ ምንነት እና አስፈላጊነት ዙርያ በፅ/ቤቱ የጉራጊኛ ቋንቋ አስልጣኝ ባለሙያዎች በአቶ ሳህሉ በረዳ እና በመምህርት ወ/ሮ ጥርርወርቅ ንጋኒ ማስገንዘቢያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል ።
በእለቱም ከወረዳው ት/ቤቶች የተውጣጡ ርዕሳነ-መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የጽ/ቤት ባለሙያዎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የእዣ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው፡፡






